ለአድዋ ጦርነት መነሳት ዋነኛ ምክንያት የሆነው የዉጫሌ ውል በሚያዚያ ፲፱፻፹፩ ዓ.ም በአሁኗ አምበሳል ወረዳ ውጫሌ በምትባል ቦታ በአጼ ምኒልክና በጣሊያኑ ንጉስ ኡምቤርቶ መካከል ተፈረመ፡፡
የውጫሌ ውል ፳ አንቀጾች ያሉት ሲሆን አንቀጽ ፲፯ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት በማጣቱ ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡
አንቀጽ ፲፯ በአማርኛ “የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከአውሮፓ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደ ወይንም ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግስታት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡
የአንቀጹ የጣሊያንኛ ትርጉም ግን “የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ሀገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል” የሚል ነበር፡፡
ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በቀጥታ በጣሊያን በኩል እንዲከናወን የሚያስገድድ ነበር፡፡
በአንቀጽ ፲፯ አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣልያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች ነው ብለው ነገሥታቱ እና መኳንንቱ ስለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ፡፡
የጣሊያን መንግስት ውሉን ለማፍረስ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ፣ የውጫሌ ውል እንዲፈርስና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሚስት የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል፡፡
እቴጌዋ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ” ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ “ይስሙ ንጉሥ!” የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይህን ንግግራቸውን ተከትሎም የውጫሌ ውል የተፈረመበት ቦታ “ይስማ ንጉሥ” በሚል ተሰይሞ እዚህ ዘመን ደርሷል፡፡
(more…) Read Full Post »