Feeds:
Posts
Comments

Archive for June, 2012

የዋልድባ ገዳም ህልውና ይከበር! 

  • “እርሶ እኛን አይወክሉንም እና ልንሰማዎትም ሆነ ቡራኬዎትን አንቀበልም” ከመነኩሳት ወገን ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
  • “ልማቱን በግድም በውድም መቀበል ይኖርባችኋል” የመንግሥት ተወካይ
  • “በዋልድባ ገዳም ምንም ድርድር አናደርግም” የአካባቢው ነዋሪ
  • በርካታ ወጣቶችም በመንግሥት ታጣቂዎች ታፍሰው ተወስደዋል
ባለፈው ቅዳሜ በዓዲርቃይ ከተማ ላይ በዋልድባ አካባቢ ሊሰራ በታቀደው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ዙሪያ የአካቢው ነዋሪዎችን፣ የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልሳዕ በተገኙበት፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የማኅበረ መነኩሳቱ ተወካዮች በተገኙበት እንዲሁም ከቤተክህነት ተወካዮች በተገኙበት የማስፈራራቱ እና በግድ የማሳመኑ ስራ እንደቀጠለ ነው። ሰሞኑን በደረሱን መረጃ መሰረት መንግስት ለልማቱ እፈልጋቸዋለው ከሚላቸው የዋልድባ ገዳም ክልል ውስጥ የሚፈርሱን መካናት የሚከተሉት ናቸው፡

  • ከአበረንታት
    • ማርገፅ ቅዱስ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን
    • ድል ሰቆቃ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን
    • እጣኑ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም  ቤተክርስቲያን
    • ሙሉ ቤት ቅዱስ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን
  • ከአባ ነፃ
    • ዲዋር ግዛ ቅዱስ ተክለሃይማኖት  ቤተክርስቲያን
    • ማይ ሸረፋ አቡነ አረጋዊ  ቤተክርስቲያን
    • አዲ ፈረጅ አብዮ እግዚ  ቤተክርስቲያን
    • ማይ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን
    • ታች እጣኖ ቅዱስተ ማርያም  ቤተክርስቲያን
    • ላይ ኩርማ አቡነ አረጋዊ  ቤተክርስቲያን
    • ጎድጓድ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን
    • ቃሊማ አቡነ ሳሙኤል  ቤተክርስቲያን
    • ቃሊማ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን
    • ቃሊማ ቅድስት ሥላሴ  ቤተክርስቲያን
    • ማይ ዓርቃይ ቅዱስ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን እና ሌሎችም ስማቸው ያልተገለጸ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚነሱ ዘገባው ደርሶናል።
ለዚህም ነው የገዳሙ መነኩሳት ይልቁንም በሰቋር ኪዳነ ምሕረት የሚገኙት መነኩሳይት (አነስት) ታላቅ ተጋድሎ እያደረጉ የሚገኙት፡፡ እንደ መነኩሳይቱ አነጋገር በመጀመሪያ እኛን ገድላችሁ መሬቱን ማረስ ትችላላችሁ አለበለዚያ ግን እኛ በሕይወት ቆመን ቅዱሳን አባቶቻችን በደማቸው እና በአጥንታቸው ያስከበሩት ገዳም በኛ በልጆቻቸው በአረማውያን ሊወሰድ አይችልም በማለት በታላቅ ተጋድሎ ላይ ይገኛሉ።  “. . .የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ. . .” መጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ ፳ ፥ ፫ የናቡቴ ቃል ዛሬም በእነዚህ መነኩሳይት አድሮ ለእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ያስተጋባል የአባቶቻችን ርስት እንሰጥ ዘንድ ከእኛ ያርቅ በማለት።

እንደመረጃ ምንጫችን ከሆነ በስብሰባው ዕለት የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በቦታው ተገኝተው ቡራኬ ለማድረግ ሲነሱ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል “እርሶ እኛን አይወክሉንም” በማለት ተሰብሰባዊ ገዳማውያኑ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ በከፍተኛ ደረጃ በቦታቸው ያልተገኙትን አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ ኮንነዋቸዋል፣ በተያያዘ ዜና በስብሰባው እለት የቤተክህነቱም ተወካዮች በቦታው ተገኝተው ገዳማውያኑን እና የአካባቢውን ነዋሪ ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እንደነበር እና በመጨረሻ የመንግሥት ተወካዮች ቦታው እንደውም “የአማራ ክልል አይደለም” ይህንን በቀጥታ የሚመለከተው “የክልል ትግራይ” ነዋሪ ነው በማለት የስብሰባውን መንፈስ ወደ ዘር እና ጎሳ ሲለውጡት ተመልክተዋል። እነዚሁ የመንግሥት ተወካዮችም በግድም ይሁን በውድ ልማቱን መቀበል አለባችሁ የሃገራችን የሥራ አጥ ቁጥሩን በ50000 ይቀንሳል  በማለት ዲስኩራቸውን መስማት ለሰለቸው ተሰብሳቢ ሲያሰሙ ውለዋል።

በመጨረሻ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ተሰብሳቢው የማኅበረ መነኩሳቱ ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በኃላ ስብሰባ አትጥሩን አቋማችን የታወቀ እና አንድ ነው የአባቶቻችንን ርስት አትንኩብን፣ አጽመ ቅዱሳኑን አታፍልሱ፣ ካልጠፋ መሬት ለምን ወደገዳማን መጣችሁብን፣ እኛ ጉልበታችን መድኅኒዓለም ነው ያሻችሁን ማድረግ ትችላላችሁ መሬቱንም ስታርሱ እኛንም ገድላችሁ መሆን አለበት በማለት ከፍተኛ የሆነ ሁካታ ተነስቶ በስብሰባው ከተሳተፉትም አንሰበሰብም በማለት በውጭ ቁጭ ብለው ከነበሩ በተለይ ወጣቶችን የመንግሥት ታጣቂዎች በርካታዎችን ጭነው ለእስር ዳርገዋቸዋል በርካቶችም ሸሸተው ወደ ጫካ እንደገቡ ከአካባቢው ምንጮቻችን ገልጸውልናል። ማኅበረ መነኩሳቱም ምሬት በተሞላበት መልኩ ነዋሪዎችን “መጥታችሁ ቅርሶቻችሁን ተረከቡን” ሲሉ መሰማታቸውንም እነዚሁ ምንጮቻችን ገልጸውናል።

መንግሥትም በማናለብኝነት አብያተ ክርስቲያኑን እንደሚያፈርስ ሲገልጽ፣ የቤተክህነቱም ተወካዮች ተባባሪ ሆነው ለአብያተ ክርስቲያኑ መፍረስ አይነተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ በሌላ በኩል የዋልድባ ገዳም ማኅበረ መነኩሳቱ፣ የአካባዊ ነዋሪ በተለይ ደባቅ፣ ዛሬማ፣ ዓዲርቃይ፣ እና አካባቢው ላይ ያሉ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች ከመንግሥት ሃህሎች ጋር ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት እየከፈሉ በሚገኙበት በዚህ ሰዓት እኛ እንደክርስቲያን አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል። በማንኛውም በጸሎትም በማቴሪያልም በገንዘብም በማንኛውም መንገድ ልንተባበራቸው እና ቅዱሱን ገዳማችንን የሊቃውንት መፍለቂያ እንዲሁም የበረካታ ዓይናማ መምህራንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንት መገኛ የሆነውን ገዳም ልንታደግ ይገባል እንላለን። 

የአባቶቻችን አምላክ ድል የማትነሳዋ የተዋሕዶ እምነታችው በእኝም በልጆቻቸው ይደርብን አሜን።

Read Full Post »


“እኔን የወደደ መስቀሌን ይዞ ይከተለኝ” 
መንግበልማት ስም ቅዱስና ታሪካዊ የሆነውን የዋልድባን ገዳም ተጠግቶ የስኳር ፋብሪካ እገነባለሁ ካለ ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ ከአገር አልፎ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በስፋት ሲያነጋግር ሰንብቷል። ዋልድባ ለክፍለ ዘመናት ታፍሮና ተከብሮበጥብቅሀይማኖታዊ ስርዓት የቆየ፣ ፍጹም ልዩ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ ዋጋ ያለው ስፍራ እንደመሆኑ በስፋት እየቀረበ ያለው ተቃውሞም በከፍተኛ ስሜት እና ቁጣ የታጀበ ሊሆን ችሏል።
                እኔም ችግሩ የአንድ ወቅት ትኩሳት ሆኖ የማይቆም፤ ይልቅስ የማንነት፣ የታሪክና የዕምነት ፅናት ጥያቄ መሆኑን በማመኔ ነበር በስፍራው ተገኝቼ ሁኔታውን መመርመር እንዳለብኝ የወሰንኩት። ያዩ፣ የሰሙትንና የታዘቡትን ለህዝብ ማካፈሉ ደግሞ የሙያ ብቻ ሳይሆን የዜግነትም ግዴታ ይመስለኛል።
                ዋልድባ ደርሼ የሆነውን ሁሉ ለመመርመር ያደረኩት ጥረት ግን በመስዋዕትነት የተከበበ፣ ብዙ ዋጋም ሊያስከፍለኝ ይችል እንነበ መሸሸግ አልችልም። ከአ.. ጎንደር፣ ከጎንደር ዋልድባ ለመድረስ ያለው የጉዞ ርዝማኔ እንዳለ ሆኖ ከገዳሙ ለመድረስ 30 በላይ ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩን ጀምሮ ያለው ጥብቅ ጥያቄና ምዝገባ ሁሉ እጅግ አስደንጋጭና ያልተለመደ ነው።

                የተሳፈርኩበት አውቶብስ ዋልድባ ሊደርስ 35 ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው ወደ ቀኝ ወደወልቃይት ቀጥታውን ደግሞ ወደ ዋልድባ የሚዘለቅበት መንገድ መገናኛ ስፍራ ላይ ትልቅ ኬላ ተሰርቷል። ይህ ስፍራ በአካባቢው ስዎች ጉምድኝተበሎ የሚጠራ ሲሆን ረቡ እና ቅዳሜ የደራ የገበያ ስፍራ እንደሚሆንም ተነግሮኛል። እዚህ ስፍራ ሲደረስ የዋልድባ ተጓዥ ወርዶ በሌላ መኪና መሳፈሩ የተለመደ ነውና እኔም ከዋልድባ መንገደኞች ጋር መውረድ ነበረብኝ። ነገር ግን ቀደም ብሎ በደረሰኝ መረጃ መሠረት እዚያ ስፍራ ላይ ያሉት የመንግታጣቂዎች ወደ ዋልድባ የሚሄዱ ሠዎችን ስም በማጣራትወዴትና ለምን?’ እንደሚሄዱ በመጠየቅ የሚመዘግቡ በመሆናቸው የእኔ እዚያ ቦታ ተገኝቶ መመዝገብ አደገኛነቱ የታሰበኝ ከመኪና ሳልወርድ ነበር።
               በመንግ አንጋቾች እጅ መውደቅ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እያሰላሰልኩ የጉዞዬን ዓላማም ጭራሽ የማላሳካበት ዕድል እንዳይፈጠር ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ ወሰንኩ። . . . በዚህም ወደቀኝ ታጥፈው ከሚዘልቁት የወልቃይት መንገደኞች ጋር ከመሄድ ውጭ አማራጭ
አልነበረኝም። በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ውስጥ በወደቀው የአካባቢው ሁኔታ እየተገረምኩ ሁሉን በፍርሃትና በጥርጣሬ አይን እየቃኘሁ ለግማሽ ቀን በወልቃይት ዙሪያመክፈልትበምትባለው የገጠር ቀበሌ ሆኜ ዋልድባን ከሩቅ በሃሳብ እየዋኘሁበት ተከታዩን ዘገባ አጠናቀርኩ።
                 በወልቃይትና በዋልድባ መካከል በሚፈሰው ዘረማ (ዛሬማ) ወንዝ መንግለስኳር ልማት እየገነባ ያለው የመስኖ ፕሮጀክት ይሄን ያህል እንዴት ትኩረት ሊሰጠውና እንዲህ ሊያጨቃጭቅ ቻለ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢና ታዊም ይመስለኛል። ዋልድባ ሲባል እንደ ደብረ ሊባኖስ፣ ዝቋላ አቦ፣ ግሸን ማሪያም….ወዘተ በአንድ የተወሰነ ጠባብ ቦታና አጥር የተከለለ የሚመሰላቸው ሠዎች ጥቂት አይደሉም።
                  ዋልድባ ገዳምን ከበው ከያዙት (ከሚያዋስኑት) ወንዞች መካከል በምእራብ አቅጣጫ የሚገኘው ዘረማ ወንዝ አሁን ለስኳር ልማት ተብሎ የመስኖ ፕሮጀክት የተጀመረበት ነው። ይህንኑ ፕሮጀክት በሚመለከት ያነጋገረኩት አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ቅዱሳን አባቶች የሚጠልቁት ወንዝ በመሆኑ መንግስት ለስኳር ልማት መስኖ ፕሮጀክት መጠቀሙ መንፈሳዊነቱን ይጻረረዋል ብሎኛል። በገዳሙ ዙሪያ ከሚኖሩ መነኮሳት መካከል አንዱ የሆኑ አባት ግን «ቅዱሳት አባቶች ከማየ ዮርዳኖስ እንጂ ከዘረማ አይጠልቁም» ብለውኛል።
                  በገዳሙ አዋሳኝ ከሚገኘው ዘረማ ወንዝ ተጠልፎ እየተስራ ያልውን የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በሚመለከት ያነጋገርኳቸው ሌላ አባት ደግሞ የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ከገዳሙ ውጪ የሚገኝ ቢሆንም ዘረማ ወንዝ በቅዱሳን መነኮሳት ዘንድ ከገነት የሚፈስ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑባይነካ ነበር ደግብለውኛል።
                  በወልቃይት እና በዋልድባ ገዳም አማካኝ ስፍራ ላይ የሚፈሰው የዘረማ ወንዝ ለአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን ውሃ የሚያጠጡበት፣ ራሳቸውም እየጠለቁ ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚጠቀሙበት እንደሆነ የገለጹልኝ አንድ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው የሰኳር ልማት ፕሪጀክቱ ከገዳሙ ውጪ ያለ ቢሆንም ከስኳር ልማቱ ጋር በተያያዘ የሚመሰረተው መንደር የአካባቢውን ሠላማዊነት ሊረብሸው እንደሚችል ገልጸው ለፕሮጀክቱ ስራ ተብሎ በሚመሠረተው መንደር የሚሠፍሩት
ሠዎች የመሃል አገር ሰዎች መሆናቸውና የአካባቢውን ጥብቅ መንፈሳዊ ህግጋት የማያውቁ መሆናቸው መጪውን ጊዜ እንድንናፍቀው አያደርገንም ብለዋል።
                 በዋልድባ ገዳምና የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ በሚሰራበት ስፍራ መካከል ርቀት መኖሩን የተረዱ ሠዎች ቁጥር በርካታ ቢሆንም ግንዛቢያቸው ከስጋት ነፃ አይደለም። ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው መንደር ከመንደሩም ጋር ተያይዞ የሚመጡ ሰዋዊ ባህሪያት የሚፈጥሩት ያልተገባ ድርጊት በርቀትም ቢሆን የገዳሙን መለኮታዊ መልክ ሊረብሸው ይችላል የሚል ስጋት አለ። እዚህ ቀደም ብለን ያነሳነው አንድ ጥያቄ ተመልሶ ሊነሳ ይችላል።የዋልድባ ጉዳይ ይሄን ያህል እንዴት ትኩረት ሊሰጠውና ሊያጨቃጭቅ ቻለ?’ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመሻት አጠቃላዩን የገዳሙን ሁኔታ መቃኘቱ ተገቢ ይመስለኛል።
መል ምድራዊ አቀማመጥ 
              ዋልድባ በአራት ወንዞች የተከበበ/የታጠረ ቢባል ይሻላል/ አራት ማእዘን አይነት ቅርጽ ያለው የአንድ ወረዳ/አውራጃ/ ግዛት ያህል ስፋት ያለው አካባቢ ነው። በሌላ አገላለጽ ከደቡብ እስከ ሰሜን/ ከአርማሕ ደጋ እስከ ተከዜ/ ያለው ርቀት በግምት 120-150 ኪሎ ሜትር ሲሆን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ማለትም ከእንስየ ወንዝ እስከ ዘረማ ወንዝ ያለው ርቀት ደግሞ ከ60-70 ኪሎ ሜትር ይሆናል።
              እንደዛም ሆኖ የዋልድባ ገዳም በደቡብ ሰፋ ያለ ሆኖ ወደ ተከዜ ወንዝ እየተጠጋ በመጣ ቁጥር እየጠበበ ሄዶ እስከ 30 . ይሆናል። አራቱ የዋልድባ አዋሳኝ ወንዞች በምስራቅ እንስየ፣ በምዕራብ ዘረማ፣ በሰሜን ተከዜ፣ በደቡብ ወይባ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ትንሹ ወይባ ሲሆን በዋልድባ ደቡብ ካሉ ተራሮች ተነስቶ ጨው በርንና ዋልድባን እየለየ የተወሰነ ርቀት ከተጓዘ በኋላ ወደ እንስያ ይቀላቀላል።
              “እህል አይቀመስበት፣ ሓጢያት አይሻገርበትየተባለለት ዋልድባ በውስጡ ወይና ደጋና ቆላማ የአየር ንብረቶች ያካተተ በመሆኑ በቦታው የሚበቅሉ ዕጽዋት አይነት ቁጥር እጅግ በርካታ ናቸው። ለአብነት ያህል ደቅማ፣ ማቅማ፣ ጣበሌ፣ ወይባ፣ ዲማ/ፍርጣጣ/ ሸመል፣ እንኮይ፣ግራር/ሦስት አይነት/፣ወይላሆ፣ በትረ ያሬድ፣ አምፋር፣ አጋም፣ ኮርች፣ ወዘተ በዋልድባ በብዛት የሚበቅሉ ናቸው። ከትላልቅ ዛፎች በተጨማሪ ቁጥራቸው የበዛ የሐረግና የሣር አይነቶችም ይበቅላሉ።
             በሃገራችን ውስጥ ካሉት ከሁለት ጥንታዊያን ገዳማት መካከል የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ከሚለዩባቸው ነገሮች አንዱ የሚለሱት የልብስ ቀለም አይነት ነው። ሁሉም በወይባ ዛፍ ልጥ የተነከረ ቢጫ ልብስ ነው የሚለብሱት። አንድ አባት ጠይቄ እንደተረዳሁት የዋልድባ መነኮሳት ነጩን አቡጅዲድ ጨርቅ በውሃ በተፈላ የወይባ ዛፍ ልጥ እየነከሩ ወደ ቢጫነት የሚለውጡት በሁለት ምክንያት ነው።የመጀመሪያው ራሳቸውን ከአካባቢው ለማመሳስል (ከሩቅ ላለመታየት) ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ግን አካባቢው ወባማ በአካባቢው አጠራር «ንዳድማ» በመሆኑ በወይባ የተነከረ ጨርቅ የወባ ትንኝ ስለማይጠጋው ከወባ በሽታ ለመከላከል ስለሚረዳ ነው። ይህንን ሚስጥር ግን ብዙዎቹ አያውቁትም።
             ሁለተኛው የዋልድባ ታሪካዊ ዛፍ ዲማ ነው። ዲማ እጅግ በጣም ወፍራምና ረዥም የሆነ (አንዳንዴ የዛፉ ግንድ ውፋሬ ከመለስተኛ ቤት ይበልጣል) የሚበላ ፍሬ የሚያፈራ ግዙፍ የዛፍ አይነት ነው። እንደዛም ሆኖ የዛፉ ግንድ የተደራረበ ቅርፊት (ልጥ) እንጂ የሚፈለጥ፣ የሚሰነጠቅ ጠንካራ እንጨት የለውም። በመሆኑም ለቤትም ሆነ ለቁሳቁስ መሥሪያነት አያገለግልም። ይሁን እንጂ ዲማ በዋልድባ የተለየ ጠቀሜታ አለው። አባቶች ወደ ብቃት ደረጃ በሚሸጋገሩበት ግዜ ግንዱን ይቦረቡሩና (በቀላሉ ስለሚቦረቦር) ውስጥ ገብተው ቁጭ ይላሉ። በዚህ መልክ ሱባኤ የሚይዙ አባቶች በሳምንት አንዴ ብቻ ነው ቋርፍ የሚመገቡት።
ከሁሉ የሚገርመው በዚህ አይነት ሆነው (ኩርምት ብለው እንደተቀመጡ) እስከ 40 አመት በሕይወት የቆዩ አባቶችና እናቶች እንደነበሩ አስረጂው ስማቸው በክብር ተመዝግቦ መገኘቱ ነው። የዲማ አስገራሚነት ለመነኮሳቱ እንደ ቤት ሆኖ ማገልገሉ ብቻ አይደለም። አባቶች በዚህ ሁኔታ እንዳሉ ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ጊዜ የተቦረቦረው የዛፍ ክፍል በራሱ እየሞላ ይሄድና መቃብር ይሆናቸዋል። በዚህ መልክ የቅዱሳን አፅም በሆዳቸው እንደያዙ የቆሙ በርካታ የዲማ ዛፎች አሁንም አሉ። ከዲማና ወይባ ሌላ ለተለያዩ ቁሳቁስ (መቁጠሪያ፣ መቋሚያ፣ ሙቀጫ፣ ጭልፋ፣ መስቀል. . .ወዘተ) መስሪያ የሚያገለግሉ የዕፅዋት ዓይነቶችም አሉ።
              ዋልድባ በደን የተሸፈነ በመሆኑ በውስጡ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የዱር እንሰሳት ያለ ስጋት የሚርመሰመሱበት፣ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው አእዋፍ የሚኖሩበት የገነት አምሳያ ቦታ ነው። አንበሳ፣ ነብር፣ አጋዘን፣ ወንድቢ(በሬ መሳይ) ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ስስ፣ አሳማ፣ ጃርት፣ ተኩላ፣ ዥግራ፣ ቆቅ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ፣ ዘንዶ፣ አዞ(ውንዝ ውስጥ) ይገኛሉ።አንዳንዴ በዋልድባም ይዘፈናልየሚባል ዝነኛ
አባባል አለ። ብሂሉ ከዱር እንሰሳት ጋር የተያያዘ ታሪክ ያለው ነው። ከጥንት ጀምሮ በዋልድባ ክልል ውስጥ ጥይት ተኩሶ እንሰሳ መግደል፣ በወጥመድ የዱር እንሰሳ መያዝና መግደል ፈፅሞ የተከለከለ ነው። ቢሆንም ከዋልድባ ባሻገር ያሉ ቦታዎችም በደን የተሸፈኑ ስለነበሩ አዳኞች ከሩቅ ቦታ እየመጡ በአካባቢው ያድኑ ነበር።
             በተለይ ደግሞ ዝኆኖች በብዛት በክልሉ ይገኙ ስለነበር ነገስታት ሳይቀሩ ለአደን ወደ አካባቢው አዘውትረው ይመጡ ነበር። ታዲያ በዋልድባ ውስጥ ገብቶ ማደን ባይቻልም ነገስታቱና ሹማምንቱ ሰራዊታቸውን ወደ ገዳሙ ክልል በማስገባት በውስጡ ያሉትን ዝኆኖች በመረበሽ ከገዳሙ ክልል እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ ጠብቀው ይገድሉዋቸው ነበር። ዝሆንን አድኖ ለመግደል ጊዜ ስለሚጠይቅ ነገስታቱ አደናቸውን እስኪያከናውኑ ድረስ በአካባቢው ድንኳን ተክለው ይቀመጣሉ።
            በዚህ መካከል በለስ ሲቀናቸው በድንኳኖቻቸው ሆነው /ዋልድባ ድንበር/ ይሸልላሉ ፣ይዘፍናሉ፣ያዘፍናሉ። በዚህ መነሻነት ነው አንዳንዴ በዋልድባም ይዘፈናል የተባለው።
      ታሪካዊ አመጣጡ
 በዋልድባ ውስጥ ሦስት ገዳማት ይገኛሉ እነርሱም
1/ ዋልድባ አብረንታንት
2/ ዋልድባ ድልሽህ
3/ ዋልድባ ስቋር ይባላሉ።
            ከእነዚህ መካከል ትልቁና አንጋፋው ዋልድባ አብረንታንት ነው። ይህ ገዳም(በገዳምነት በይፋ የተቋቋመው 1398 . ) ሲሆን 485 . ጀምሮ ግን መናንያን በቦታው ይኖሩ እንደነበር ይታመናል። ዋልድባ ድልሽህና ዋልድባ ሰቋር ግን በቅደም ተከተል 1505 . እና 1658 . ነው የተመሰረቱት። በዋናው አብረንታንት ገዳምና በሁለቱ መካከል ያለው ርቀትም ቢሆን ትልቅ ነው። ለምሳሌ ያህል ከዋልድባ አብረንታንት እስከ ዳልሽህ ያለው ርቀት 50 . ይሆናል። ዋልድባ ከስፋቱ በተጨማሪ በበርካታ አስደናቂ ነገሮች ከሌሎች ገዳማት ይለያል። የዋልድባ መነኮሳት በልብሳቸው ብቻ ሳይሆን በአመጋገባቸውም ይለያሉ። ገዳማውያኑ የጣመና የላመ ምግብ ብቻ ሳይሆን ከሙዝ፣ ከተልባ፣ ከጨውና ከኑግ በስተቀር የእህል ዘር አይመገቡም። ከሙዝና ከኑግ የሚሠራውን    መብልቋርፍይሉታል።
በዋልድባ ከሙዝና ከኑግ የተሰራ የቋርፍ ምግብ መብላት የተጀመረው 1566 .. ጀምሮ ነው። ከዛ በፊት መናኒያኑ ይመገቡት የነበረው ጣብሌ፣ ገመሎና ሳዳ ከተባሉ ዕፅዋት ስር የሚዘጋጅ መራራና ጎምዛዛ ቋርፍ ነበር።
         በነገራችን ላይ ሙዙን የሚመገቡት ገና ሳይበስል በጥሬው እያለ በመቁረጥና በመቀቀል ነው። ሙዙን ቀቅለውና በቋንጣ መልክ አዘጋጅተው ያስቀምጡታል። በዚህ መልክ በጥንቃቄ የተዘጋጀው የሙዝ ቋንጣ ሳይበላሽ እስከ ሰባት ዓመት ይቆያል። በዋልድባ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አራት ትላልቅ ወንዞች በተጨማሪ ሙዝ የሚመረትባቸው 30 ወንዞችና ምንጮች ይገኛሉ። በእነዚህ ቦታዎች እንደ ልማት ቦታው ስፋት መነኮሳት ተመድበው የመስኖ ሥራና ንብ የማነብን ተግባር ያከናውናሉ። በዋልድባ በመስኖ ስራ የተሰማራ መነኩሴወንዘኛይባላል። በዋልድባ ማር የሚመረት ቢሆንም (ያውም ምርጥ ማር) መነኮሳቱ አይጠቀሙበትም (አይመገቡትም) ለገበያ ወጥቶም አይሸጥም። ይልቅስ የበሰለ ሙዝና ማር ገዳሙን ለመሳለም ለሚመጡ እንግዶች (ምእመናን) ብቻ ነው የሚሰጥ። ያም ሆኖ ግን በዕድሜና በስራ ምክንያት ደክመው ለተኙ መናንያን ከድቁስ ጋር ተበጥብጦ የሚሰጥበት ጊዜ አለ። በሰሙ ግን ጧፍ በማዘጋጀት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም ይተርፋሉ።
           በሌሎች የኢትዮጵያ ገዳማት የማይገኝና የዋልድባ ብቸኛ መለያ ከሆኑት አንዱስምረትየሚባለው ርዓት ነው። ስምረት ባጭሩ የሳሙኤል ልጅነት የሚገኝበት ርዓት ማለት ነው።(አቡነ ሳሙኤል የመጀመሪያው የገዳሙ አበመኔትና ጻድቅ ናቸው።) እንደ ምንኩስና ሁሉ ስምረት በከባድ ጸሎትና ስግደት የታጀበ የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው። ይሁን እንጂ በዓመት ውስጥ ሥርዓተ ስምረት የሚፈፀምባቸው ቀናት የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ ቀናትም ለወንድ ሐምሌ 5 ቀን ሲሆን ለሴቶች ደግሞ የካቲት 16 ቀን ናቸው። ይሁንና እንደ አጋጣሚ ሐምሌ 5 ቀን ወይም አርብ ከዋለ የወንዶቹም በየካቲት ይከወናል።
         ሴት መነኮሳይት ወደ ቤተ መቅደስ (ገዳሙ ውስጥ) መግባት ስለማይችሉ ሥርዓቱ የሚፈጸምላቸው ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ (ማየ ዮርዳኖስ ሳይሻገሩ) ካለው ቦታ ነው። ቡራኬ ለመቀበልም ሆነ ለማስቀደስ ሲፈልጉ ከቤተ መቅደሱ 300 ሜትር ያህል ርቀት ላይ ቆመው ነው የሚያስቀድሱት። በተረፈ ወደ ገዳሙ ለመምጣት ለማይችሉ አንዳንዴም ለማይፈልጉ መነኮሳትና መነኮሳይት ማይለበጣ እና አባ ነፃ እየተባሉ ከሚጠሩ ስዕል ቤቶች ርዓቱ ይፈፀምላቸዋል። ስዕል ቤት
የሚባለው ታቦተ ህግ የሌለበት ማህበረ መነኮሳቱ በጋራም ሆነ በግል ፀሎት የሚያደርጉበት የተለየ ቤት ማለት ነው።
         ሴት መነኮሳይት በዋልድባ መኖር የማይፈቀድላቸው ቢሆንም ከገዳሙ ክልል ውጪ ለሴቶች ተብለው የተዘጋጁ ቦታዎች አሉ። እነርሱም ጉብታ፣ ማይ፣ ሐርገፅ(የአዞ ወንዝ) እና ቤት ሞሎ ይባላሉ። በዐጼ ባካፋ ዘመን የወልቃይትና የጠገዴ ባላባትና ገዢ የነበሩት ደጃዝማች አያና እግዚእ ያሰሩት ታሪካዊ ግንብ የሚገኘው ከሶስቱ የሴት መነኮሳይት መኖሪያ አንዱ በሆነው በሞሌ ነው።
              ቀደም ሲል በገዳሙ የተለያዩ የዱር እንሰሳት እንደሚገኙ ገልጫለሁ። በዋልድባ ደግሞ በገዳማቱና ቤተ መቅደሶች ዙሪያ ከሚኖሩ መነኮሳት ይልቅ በግላቸው በየጫካው በፅሞና የሚኖሩ በቁጥር ይበልጣሉ። እንደዛም ሆኖ የዱር እንሰሳቱ (አውሬዎቹ) ስምረት የገባ መነኩሴን ፈጽሞ አይተናኮሉም። መነኮሳቱም ቢሆኑ አደጋ ያደርሱብናል ብለው አይሰጉም። አንድ የከብት እረኛ በከብቶች መካከል ያለስጋት እንደሚያልፍ ሁሉ መነኮሳቱም በነጻነት በአንበሳና በነብር መንጋ መካከል ይዘዋወራሉ። የተኛ ዘንዶም ተሻግረው ይሄዳሉ።
              አባቶች እንዳወጉኝ ከሆነ አልፎ አልፎ (ለፈተና) አንበሳ መነኩሴውን የሚያልፉበትን መንገድ ጠብቆ ከመንገድ መካከል በመተኛት አላሳልፍም የሚልበት አጋጣሚ አለ። በዚህን ጊዜ መነኩሴው ሥርዓተ ስምረት በሚቀበሉበት ወቅት የተገለጸላቸውን ልዩ ቃል መጠቀም ይኖርባቸዋል። የዚህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው መነኩሴ “ግፍአ አበው” ሲሉ አንበሳው ጅራቱን እንደ ለማዳ ውሻ እየወዘወዘ ተነስቶ ይለቅለታል። ግፍአ አበው ወደ አማርኛ ሲመለስ “በአባቶች አምላክ” እንደ ማለት ነው።
            በተረፈ በዋልድባ የስምረት ሥርዓት ያልተፈፀመለት መነኩሴ (ጳጳስም ቢሆን) ማየ ዮርዳኖስ አይቀዳም። በገዳሙ አይቀድስም። አይቆርብም። ቢሞትም ከአበው መቃብር አይቀበርም። እንግዲህ የዋልድባ ገጽታ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል። የአይነኬነቱ መሠረቶች፣ የአይደፈሬነቱ ምስክሮች እኒህ ናቸው። የአነጋጋሪነቱ ዓይነተኛ ምክንያትም ይህ ፍጹም የሆነው መንፈሳዊነቱና ታሪካዊነቱ ነው።
ይቆየን።

ሙሉውን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Read Full Post »

VOA June 14, 2012

ዛሬ ዛሬማ ላይ ሊካሄድ የነበረው ስብሰባ በዛሬማ ነዋሪ ወጣቶች ከባድ ተቃውሞ ምክንያት ወደ ዓዲርቃይ የተዛወረው ስብሰባ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ የመንግስት ተወካዮች፣ የገዳሙ ተወካዮች፣ እንዲሁም ጥቂት ገዳማውያን እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት መንግሥት ልማቱን አትቃወሙ በማለት ለማስፈራራት የሞከረበት ስብስበባ እንደነበር ከእማኞች ለመረዳት ችለናል። አባቶችም ይልቁንም የሰቋር ኪዳነ ምሕረት እናቶች በወኒያቸው ኮርተናል “አባቶቻችን በደማቸው ያቆዩልንን ርስት፣ ቆመን እያየን ሊወሰድ አይችልም” “መጀመሪያ እኛን ገላችሁ” በማለት ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል።
የሃገረ ስብከቱም ሊቀ ጳጳስ “ልማትን አትቃወሙ” ማለታቸው በመነኩሳቱ ዘንድ ከባድ ቁጣን አስነስቶባቸዋል

Read Full Post »

በዋልድባ ገዳም ዙሪያ እስሩ፣ እንግልቱ፣ እንዲሁም ማስፈራራቱ እንደቀጠለ ነው. . . የገዳማውያኑን የምዕመኑን ጩኽት
የሚሰማ ጠፋ. . . ቤተክርስቲያንም አባት አጥታለች፣ ኢትዮጵያም የሕዝቡን ጩኽት የሚሰማ መሪ አጥታለች ታዲያ ምን ይሻላል?

savewaldba@gmail.com

Read Full Post »

ባለፈው ሰኞ ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓም ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ደብዳቤዎችን ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟቻቾች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ ለአሜሪካን የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ለተለያዩ ሴናተሮች፣ ኮንግረስ ተወካዮች በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ለኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ሎስ አንጀለስ፣ ለኢትዮጵያ ዮናይትድ ኔሽንስ አምባሳደር ደብዳቤዎችን አስገብቷል። ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑት ድርጅቶች መልሶችን በቅርቡ ይጠበቃሉ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥትም መልሶችን እንደሚጠበቁ ተነግሮናል እንደደረሰን እንዘግባለን

ለተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች የተላከውን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
ለኢትዮጵያ ኤምባሲ የተላከውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Read Full Post »

ያልተጻፈ የማይጻፍ ያልታየ ያልተዘገበ
          ምን አለና ነው ያልተነበበ
                   ገና ድሮ ጥንት በዘፍጥረት  በህገ ልቦናው
                   አዳም ከገነት የወጣ የተባረረው
                   የሞት ሞትን ሞቶ ከመቃብር የወረደው
                   ሄዋን ከክብር ወደ ጥልቅ የወረደችው
                   የአምላክን ትእዛዝ መርሳት መዘንጋቱዋ ነው
                   ያልተገባውን ስራ መፈጸሙዋ ነው
ታሪክ እራሱን እየደገመ ታሪክ ሆኖ ቢያልፍም
ያማይልፍ መስሎ በጊዜው ህዝብን ቢያስጨንቅም
ማለፍ ግን አይቀርም ይሄዳል
ጠባሳውን ጥሎ ባአዲስ ዘመን ይተካል
ዛሬም ታሪክ ራሱን ይደግማል

                   ጥንት ኤሳው የወደቀበትን
                   ሃብት ንብረት ተሩፋት  ያጣበትን
                   በሆዱ ተታሎ የተደለበትን
                   የእቆብ በክብር ድል የነሳበትን
                   ታግሎ ጥሎ ያገኘውን
                             የብኩርናን ክብር ሊያሳጡ
                             የበኩሮቹን በኩር ከልባችን ሊያወጡ
                             መንፈሳዊ ክብሩን አስዘንግተው
                             ንጹህ ምንጩን አደፍርሰው
                    ያንን መራራ ውሃ ሊያጠጡን
                   ውሃችንን መሪባ ውሃ ሊደርጉብን
                   ክብራችን ማንነታችንን  ሊነፍጉን
                   ተነሱ ዛሬም ሰይፋቸውን አነሱብን
                   ርስታችንን ለባእዳን አሳልፈው ሰጡብን
                   ባገራችን ስደተኛ መጻተኛ አደረጉን
           መነኮሳት ሳይታፈሩ ካህናቱ ሳይከበሩ
          ጎልማሶች አንእስት እንደሰው ሳይቆጠሩ
          ሲገፉ በአላውያን በግፍ ሲገፈተሩ
          አየናቸው ሲደግሙ ታሪክ ሲያመሰጥሩ
          የጥፋት አባቶቻቸውን ሲዘክሩ
በሄዋን ገላ የተሰወረው እባብ በክፋት                 
የህይወት በለስን ያስቀጠፋት
ዛሬም   የዘመኑ ሌጊወን
አሳድጎ አብዝቶ ልጆቹን
መጣ ለጥፋት ሊፈትነን
በልጆቹዋ ተመስሎ ገላውን አለስልሶ
አስመስሎ የበግ ለምድ ለብሶ
ልማት እያለ ፍሬ እናፍራ
እድገት ኢያለ ወሬ እያወራ
መጣ በድፍረት ሊያጠፋው
ርስታችን ያለ ዋጋ ሊያስቀረው
ዋልድባ ዋልድባ መሆኑን ዘነጋው
ያ የያዘው  ክፉ መንፈስ ልቡን ስለነሳው
ታሪክን ጠብቆ ማቆየት
ትውልድን ከትውልድ ማገናኘት
ህዝብን ከፈጣሪ ማስታረቅ
የክፉውን መንፈስማድቀቅ
                   በስነምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ
ንጹህ ዜጋን መፍጠር ማብቃት ለወግ
          ይህ ሁሉ በጎ ስራ እንደጥፋት ሆኖ  
          መልካም ማድረግ እንደወንጀል ገኖ
          ክስ ሆነባት ጥፋት
          እንደ መርገም ቆጠሩባት
የቆሙበትን ምድር እየረገሙ
ያረፉበትን መሬት እያደሙ
           ውለታዋን ዘንግተው በጎነቱዋን ረስተው
          ሊጠፉዋት መጡ ጦር ሰብቀው ዝናር ታጥቀው
          ያለፍርሃት በድፍረት ጉልበት አለን ብለው
እያወቁ እናዳላዋቂ ቢሆኑም
ታሪክን አንብበው ባይረዱትም
 ራእይ ህልማቸው ጥፋት ቢሆንም
መሽቶ ሲነጋ ግን ድል መሆን አይቀርም
ቢታመኑ በሰረገላ በጉልበታቸው     
ዘመን ተገልብጦ  ሃይል ቢሰጣቸው
          ትንቢቱ ሲፈፀም የአምላክ ቃል ኪዳኑ
          ቀኙን ሲዘረጋ ሲበራ ብርሃኑ
ይጣፋሉ እነርሱ ጉሙ ይገፈፋል
ያምላካችን ማዳን  በግልጽ ይነገራል
ዋልድባ አብረንታንት ዘላለም ይኖራል
ድንቅ ስራው ሁሉ ሲወሳ ይኖራል
እንደጥላ የሚያልፍ  ስልጣንን አለን ብለው
                    ወንበራቸው ጋሻ  ሃይል ሆኖላቸው
መንበሩን ቢነኩ በግፍ ቢደፍሩት
                              ቅዱሱን ቦታ አርሰው እሾህ ቢያበቅሉበት
                    የክፋትን ፍሬ ዘር ቢዘሩበት
                    እሾህ አሜኬላን አረም ቢያበዙበት
           የክፋትን ጥሪት ጎተራ ቢያስገቡት
 ወግማረጉን አሳጥተው ቢከትሙት
የቀደመክብሩን ቢነፍጉት
ዋልድባ ዋልድባ ነው
መሰረቱ አለት ንጹህ ደም ነው
ቀን ጊዜ ወራት ዘመን የማይሽረው
ማህተሙ በክብር የታተመው
ዋልድባ የሚለው ቃል የተፃ ፈው
በደም ቀለም ክታብ ነው
በሰማእታት ባባቶች ጸሎት ቡራኬነው
ዋልድባኮ ዋልድባ ነው ባለጊዜ የማይጥለው
ዘመን ቀናት ያልበገረው
          ጸሃይ ለባለግዜወች አድልታ
          ብርሃኑዋን ነፍጋን ተቆጥታ
          ለጥፋት  ተባባሪ ብትሆንም
          የመቅደስ መፍረስ ባይገዳትም
ዛሬ ባይሆን ነገ ሲነሳ እያሱ
በጸሎት ምህላ ሲከፈት መቅደሱ
ስልጣኑዋ ተነፍጎ ባለችበት ስትቆም
የሃፍረትን ሸማ  በአርምሞ ስትቆም
አሁን እናያለን በርቱ ክርስቲያኖች
የኢቶጵያ አኝታ የቁርጥ ቀን ልጆች
          የክረምት ጨረቃን ተከትለው ወጥተው
          እውነት ብርሃኑዋ ያዛልቃል ብለው
          የክረምት ጨረቃ ትርጉሙ ጠፍቶዋቸው
          ማሰተዋል ጥበቡ ተሰው ሮባቸው
ሊነጋ ሲል ጨልሞ በድቅድቅ ተውጠው
ተስፋ ያደረጉዋት ጨረቃ ረስታቸው
በአውሬየተበሉ እጅግ ብዙ ናቸው 
የክረምት ጨረቃ ሳይነጋ ከድታቸው
          ላታዛልቅ ቀድማ ወጥታ
 ብርሃኑዋን አሳይታ
          አባብላ በስሜት  አስኮብልላ አስወጥታ
          ስንቱን አስቀረችው ካልሆነ ስፍራ ካልሆነ ቦታ
አሁንም ዛሬ የተከተላችሁዋት
አምናችሁ እሱዋን የወጣችሁ የምታመልኩዋት
እባካችሁ ካለፈው ተማሩ
እንደወጣችሁ እንዳትቀሩ
ዋልድባ እኮ ዋልድባ ነው
ዘመን ግዜ የማይሽረው
          ለክብር ለመብቃት ካሰባችሁ
          ሰማእትነቱን ለመቀበል ከወሰናችሁ
          ከውስጥም ከውጭም ተገፍተን ተዘልፈን  
          የክፉወችን ወሬ በፍጹም ታግሰን
          ነገሳይሆን ዛሬ መነሳት አለብን
ምንመም እንኩዋን አምላክ ዝምቢልም
ምላሹን ለመስጠት ድምጹን ባያሰማም
ቃልኪዳን ስላለን በእምነት የከበረ
ሃይማኖት ስላለን በገድል የታጠረ
የባቶች አበውን ፍኖት ተከትለን
ዛሬ ባይ ሆን ነገ መፈጸሙን አውቀን
ነገ ሳይሆን ዛሬ መነሳት አለብን
          ክፉን ለመቃወም ክፋትን ለማስቆም
          መንገዱን ክፈቱ ካህናቱ ምሩን
መለከቱ ይነፋ ይጎሰም ነጋሪት
                    አዋጁን አውጁ ህዝቡንም አበርቱት
                    ውጡ ለሰአታት ቁሙ ለማህሌት
                    አውጡት ጸናጽሉን ከበሮውን ምቱት
ምህላ ጸሎቱን ዛሬውኑ አውጁት
ዋልድባን ታደጉ ልባችሁ ይከፈት
ምሩ መንገዱን አሳዩን
          እምቢ ብትሉ ግን ዛሬ ባትነሱ
          የሃሰትን እንባ ለቅሶ ብታለቅሱ
          ቸለል ብላችሁ ዋልድባን ብትረሱ
          ታሪክ ይፈርደናል ያስተዛዝበናል
          ጸሃይ የወጣችለት ትንሳኤ ይሆናል
ባለ በገና መዝሙረኛው
ክፉ መንፈስ ቀጥቅጦ የገዛው
አጋንንትን አስሮ ገደል የጣላቸው
ሰባት ሃብታት የተቸረው
ስለ እየሩሳሌም ሲናገር ሲያመሰጥር
ስለ ህልውናዋ ሲ,መመሰክር
          ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ነው ያለው
          ስለቅድስት ሃገሩ ግድ ቢለው
         
           
           
         
           
           

Read Full Post »

  • ዋልድባ የጸሎት ቦታ እንጂ የኢንቨስተሮች አይሆንም!
  • መንግሥት እጆቹን ከቤተክርስቲያን ላይ በአስቸኳይ ያንሳ!
  • የኢትዮጵያ ገዳማት ህልውና ይከበር!
  • መንግሥት የቤተክርስቲያኗን መብት መጋፋት በአስቸኳይ ያቁም! 

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ስለ ዋልድባ ብዙ ነገሮችን ከአንባቢያን ጆሮ ማድረሳችን ይታወሳል፥ አሁንም በዋልድባ ዙሪያ በመንግሥት ሃይሎች ዋልድባ ገዳምን እና አካባቢውን በማናለብኝነት እያረሰ እና አጽመ ቅዱሳኑን በማፍለስ የስኳር ፋብሪካውን ግንባታ እናደርጋለን በማለት ሥራውን በከፍተኛ ፍጥነት እያካሄዱ እንደሆነ ከአካባቢው የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፥ ዋልድና ገዳም ውስጥ ያሉትም አባቶችን መንግሥት በተለያየ ዘዴ ተጠቅሞ ከአካባቢው ለማስወገድ ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። እናንተ ለተቃዋሚዎች የምትሰሩ ጸረ ልማት እና ጸረ ሰላሞች ናችሁ፣ ስኳር ስለተወደደ ስኳር ቢለማ ምናችሁ ይነካል በማለት ማዋከቡን ቀጥሏል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ጊዜያዊ ኮሚቴ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠራው የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ጥሩ ምላሽ ማግኘቱን ከተለያዩ ከተሞች በቦታው የተከታተሉት ዘግበውልናል፣ ትላንት ጠዋት ከጠዋቱ 8:00 am. ጀምሮ በሁናይትድ ስቴትስ ሕህ መወሰኛው ምክር ቤት ፊት ለፊት የተሰባሰቡት የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ነዋሪዎች ከተለያየ የአሜሪካን ግዛቶች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ተደርጓል፣ ከነዚህም ግዛቶች መካከል ዋነኛዎቹ ቦስተን፣ ሻርለት ኖርዝ ካሮላይና፣ ቺካጎ፣ ሜኖሶታ፣ አትላንታ፣ ፊላደልፊያ፣ እንዲሁም የኒው ዮርክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ተገኝተው መንግሥት እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ የታሪክ እና የሃይማኖት ማጥፋት ዘመቻ በጥብቅ ተቃውመዋል።
  በዚህ ገዳም ላይ ደረሱ ከተባሉት አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ለስኳር ፋብሪካ ፕሮዤክትና ለሸንኮራ-አገዳ ልማት ቦታው እየታረሰ ነው፤ የአበው መካነኩሳት አረፈ አጽማቸው እየተቆፈረ እና እየፈለሰ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰደ ይገኛል፣ አያሌ አብያተ-ክርስቲያናት ሊፈርሱ በዕቅድ ተይዘዋል፣ የገዳሙ ንብረት የሆነ በርካታ ገንዘብ ባልታወቁ ታጣቂዎች ተዘረፈ፣ ብዙ ኲንታል የእጣን ምርት ባልታወቁ ሰዎች ተቃጠለ፤ እናም ይህን አባቶች «በደል» ያሉትን በዝርዝር ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚገልጹ መነኮሳት አደን፣ ወከባና እንግልት እየደረሰባቸው ነው የሚሉ ይገኙባቸዋል።
VOA interview June 4, 2012

Washington DC June 4, 2012
New York City June 4, 2012

Los Angeles, CA June 4, 2012


የተባለው ልማት በእርግጥም በዕቅድ ላይ መሆኑን መንግትም ሆነ ጠቅላይ ቤተ-ክህነቱ ያምናሉ። መንግሥት፣ «ልማቱ ከገዳሙ ብዙ እርቅት ላይ ስለሆነ አይነካውም» ሲል፣ ወደ ስፍራው የተላኩት የጠቅላይ ቤተ-ክህነቱ የዐይን ምስክሮችም ይህንኑ አረጋግጠው፣ «ቤተ-ክህነት የመንግስቱን የልማት ዕቅድ ትደግፋለች” ብለዋል።

Toronto Canada June 4, 2012 by http://www.esat.com 
የገዳሙ ይዞታ እንዳይነካ ጥያቄ የሚያቀርበው ሕዝብ በአካባቢው ብቻ አልተወሰነም። «ዋልድባን ለመታደግ የተቋቋመ ዓለማቀፍ ኰሚቴ» የተሰኘው ስብስብ የየአካባቢው ተጠሪዎች ለቪኦኤ እንደገለጹት፣ ዛሬ አንድ ዓለማቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በመካሄደ ላይ ነው። ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ቶሮንቶ-ካናዳ፣ ሎስ-አንጀለስ-ላኪፎርኒያ፣ ኒው-ዮርክና ዋሽንግተን ዲሲ። አውሮፓ ደግሞ ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ብራስልስና አውስትሬሊያ መሆኑን አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል።

በትላንትናው ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት Capitol Hill ከጠዋቱ 8:00 ሰዓት የተጀመረው መረኅግብር በጸሎት በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ መሪነት ከተከፈተ ጀምሮ በኃላም በፔንሲልባኒያ ጎዳና ላይ በእግር ተጉዞ በአሜሪካው የstate department ላይ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን እና ጸሎት ተጠናቋል። በዚህም ትዕይንት ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከቦስተን፣ ከኒው ዮርክ፣ ፊላደልፊያ፣ ቺካጎ፣ ሜኖሶታ፣ አትላንታ ከሰሜን ካሮላይና ሻርለት፣ እንዲሁም ከቨርጂኒያ እና ሜሪላንድ የዲሲ ነዋሪዎችን ጨምሮ የተገኙበት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደነበር ተመልክተናል። ማለዳ ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ተነስቶ ወደ ውጪ ጉዳይ መሥራ ቤት የተጓዘውን የዋሽንግተኑን ሰልፍ ተከታትለን ነበር።
በዚህ ሰልፍ ላይ የክርስትና እምነት ተከታይ ብቻ አይደለም የተገኙት። ሌሎችም በኢትዮጵያውነታቸው ተገኝተዋል።
ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተወከሉት ባለሥጣን Ms Lora, ሙሉ ስማቸውን ማግኘት አልተቻለም፤ የሰልፈኛውን ደብዳቤ ተቀብለው ጉዳዩን እንደሚያጤኑትና ተገቢ ነው የሚሉትን ምላሽ በጽሑፍ እንደሚሰጡ ለሕዝቡ ገልጸዋል።
በተለይም ባለፈው ሐሙስ ሰቋር ውስጥ፣ በማግስቱ ዐርብ ደግሞ ገሪማ ላይ ስብሰባ ተካሂዷል። የሐሙሱ፣ እራሱ ሕዝቡ ተጠራርቶ የተሰባሰበበት ሲሆን የዐርቡ ደግሞ ባለሥልጣናት የገዳሙን አሥር ያህል መነኮሳት ጠርተው የሰበሰቡት እንደነበር ተገልጾልናል። 
በተለያየ ከተማት የተደረገውን የቪዲዮ ዝርዝር በቅርቡ እናቀርባለን።
እግዚአብሔር አምላክ ሃገራችን ኢትዮጵያን እና ቤተክርስቲያንን በቸርነቱ ይጠብቅልን አሜን

Read Full Post »

የዋልድባን ገዳም እናድን የሚሉ ሰላማዊ ሰልፎች በዓለም ዙርያ ሲካሄዱ ውለዋል

Read Full Post »

ዋልድን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ከላስ ቬጋስ እና ካናዳ ተወካዮች ጋር ያደረገው የሬዲዮ ቃለ ምልልስ ተከታተሉት። 

Read Full Post »

የVOA June 1, 2012 ቃለ ምልልስ 
በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው መንግሥት፣ ማናለብኝ በማለት ሥራውን እየሰራ እንደሆነ ይነገራል። የቤተክርስቲያኗ የበላይ አካላትም እስከ አሁን ምንም ድምጽ ሊያሰሙ ፈቃደኞች አይደሉም እስከመቼ ይሆን?
ቸር ወሬ ያሰማን።

የVOA June 2, 2012 ቃለ ምልልስ 
በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው መንግሥት፣ ማናለብኝ በማለት ሥራውን እየሰራ እንደሆነ ይነገራል። የቤተክርስቲያኗ የበላይ አካላትም እስከ አሁን ምንም ድምጽ ሊያሰሙ ፈቃደኞች አይደሉም እስከመቼ ይሆን?
ቸር ወሬ ያሰማን።

Read Full Post »

Older Posts »