Feeds:
Posts
Comments

Archive for April, 2012

READ THIS ARTICLE IN PDF.

·         ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ጉዳይ ከፓትርያሪኩ እና ከመንግሥት ጋራ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል። 
·     ማኅበሩ የወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት በዋልድባ ገዳም ላይ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ ያጠናቀረውን ሪፖርት አስመልክቶ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል::
·     “እስከ 20 ሄ/ር የገዳሙ መሬት በግድቡ ውኃ ይሸፈናል፤ ፕሮጀክቱ የገዳሙን 40% የምርት ገቢ 60% የምእመናን ድጋፍ ያሳጣዋል” (የማኅበሩ አጥኚ ቡድን ሪፖርት)::
·       ማኅበሩ የፕሮጀክቱ አካባቢ ከሚለወጥበት እስከ ዲዛየን ማሻሻያ የሚደርስ የጥናት አማራጭ እንዲያቀርብ፣ ገዳማውያኑ ስለ ፕሮጀክቱ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ያላቸው ሐሳብ የሚደመጥበት አቋማቸውንም ያለጫና የሚያሳውቁበት መድረክ እንዲያመቻች ተጠይቋል::
·        የስኳር ኮርፖሬሽኑ በፕሮጀክትና ፋብሪካ ማኔጅመንት የአቅም ማነስ ችግር እንዳጋጠመው አስታውቋል::
·     “ወደ ፕሮጀክቱ ትግበራ ከመግባታችን አስቀድሞ መነኰሳቱን እንደ መንግሥት በአለማነጋገራችን አጥፍተናል፤ እነርሱን [የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳትን] ማማከር ነበረብን፡፡” (የፕሮጀክቱ ሓላፊዎችና የወረዳው ባለሥልጣናት)::
·         መንግሥት የፕሮጀክቱን የጥናት ሰነዶች ይፋ ያድርግ (አንድ የኢንቫይሮመንታል ዲዛይን ምሁር)::
(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 19/2004 ዓ.ም፤ April 27/2012 )፦ መንግሥት በክልል ትግራይ ምዕራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ በሚገኘው የዛሬማ፣ ዱቁቆ እና ተከዜ ሸለቆ በሚያካሂደው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት የተነሣ ከአገራችን ታላላቅና ቀደምት ቅዱሳት መካናት አንዱ በኾነው በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ የተጋረጠው አደጋ ለብዙኀን መገናኛ ዘገባ ከዋለ ድፍን ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡


የሱባኤ /ጾምና ጸሎት/፣ የሕርመት /ተዐቅቦ/ እና የሥራ ቦታ በኾነው ገዳመ ዋልድባ ዐጸባውን ችለውና ታግሠው ከዚህ ዓለምና ከረቂቃን አጋንንት ጋራ እየተጋደሉ በኅቡእና በግልጽ ለሚኖሩት በሺሕ ለሚቆጠሩ ባሕታውያንና መነኰሳት የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ዋልድባን የዓለማውያን መናኸርያ፣ የከባድ መኪኖች መሽከርከሪያ፣ የነጋድያንና የሕዝብ መስፈርያ በማድረግ ሕጉንና ሥርዐቱን የሚጥስ፣ ክብሩንና ህልውናውን የሚያጠፋ ነው፡፡“በሲኖዶሱም በጳጳሳቱም የተገፋን ነን፤ መንግሥትም ለቤተ ጣዕማዎች አድልቶ ያሠቃየናል፤” የሚሉት የዋልድባ አብረንታንት ገዳም የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለመንበረ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት እና በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥትና የቤተ ክህነት አካላት ቢያቀርቡም ሰሚ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ የጸጥታ ኀይል ጥበቃ ውስጥ በሚገኘው ገዳም እግዚአብሔርን መሪያቸው፣ ጸሎትን መሣሪያቸው፣ ትሩፋትን ሥራቸው አድርገው በታላቅ መንፈሳዊ ትጋት የሚኖሩ የገዳሙ አርእስተ ባሕታውያን በዋልድባ ላይ ስለመጣው መከራ በየበኣታቸው በሱባኤ ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡

ዋልድባን በሚያዋስነው ዛሬማ ወንዝ ላይ የሚሠራው የፕሮጀክቱ ግድብ በተወሰነ ርቀት ወደ ገዳሙ የሚገባየግንባታ መዋቅር ወይም የውኃ አካል እንዳለው መነኰሳቱና የዐይን እማኝነታቸውን የሰጡ ምእመናን መመስከራቸው ተገልጧል፤ ማኅበረ መነኰሳቱን ለከፍተኛ ሐዘን የዳረገው በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ለደኅና ተጓዥ አንድ ሰዓት ያህል የሚወስድና ወደ ገዳሙ መሬት ዘልቆ የገባ የጥርጊያ መንገድ ሥራ አሁንም እንደቀጠለ መኾኑም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ይህ ጥርጊያ መንገድ ለሚገነባው ግድብ የአፈር ምርመራ ሥራ ለመሥራት የቁፋሮ ማሽኖችን ወደ ገዳሙ ለማመላለስ ካገለገለ በኋላ የተዘጋ ስለ መኾኑ ቢገለጽም ከገዳሙ 30 ኪ.ሜ የሚርቁትን የእርሻ ቦታውን፣ ፋብሪካውን፣ የ4000 ሠራተኞች መኖሪያ ቤቶችንና 120 የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን የሚያገናኙ መንገዶች አካል እንደማይኾን ለማረጋገጥ አለመቻሉ ተመልክቷል፡፡

ዓዲ አርቃይ በኩል የገዳሙን ይዞታ ለማስከበር በሚል በዋልድባ አብረንታንት ገዳም የሰቋር ኪዳነ ምሕረትንና የዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረትን በፓርክነት ለመከለል የታሰበው ዕቅድ ለጊዜው የተዳፈነ ቢመስልም ፕሮጀክቱ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገባ ከ50,000 – 75,000 ሄ/ር የሸንኮራ አገዳ ተክል በሚለማበት በመዘጋ /ሞፈር ቤቶች/የሙዝ ቋርፍ የሚዘጋጅባቸው የአትክልት ቦታዎች፣ የገዳሙ መተዳደርያ የኾኑ ሌሎች ሰብሎች የሚመረቱባቸው የእርሻ ይዞታዎች፣ እርግና የተጫናቸውና የታመሙ አባቶች የሚያርፉባቸው የማይ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የዕጣኖ ቅድስት ማርያም እና የደላስ ቆቃህ አቡነ አረጋዊ አብያተ ክርስቲያን 3.8 ቢልዮን ኩቢክ ውኃ በሚይዘው የግድቡ ውኃ መሸፈናቸው፣ በአባ ነጻ የቅዱሳን ዐፅም መፍለስና በግድቡ ውኃ የመጥለቅለቅ ስጋት ውስጥ መገኘቱ በፕሮጀክቱ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሊታዩ የሚገባቸው አካባቢዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንደነበሩ የዜና ዘገባውን ተከትለው የወጡ መግለጫዎች፣ ሞያዊ ትችቶች፣ የተቃውሞ ሰልፎችና ስብሰባዎች ያስረዳሉ፡፡

የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በመንግሥት የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረትየአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት፣ በዓለም ገበያ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከሚገነቡት 10 የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ መኾኑን የሚገልጸው የስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ፡- “ግድቡ በሚያጠራቅመው ውኃ ሳቢያ በቅዱስ ገዳሙ ላይ የሚደርስ ጉዳት እንደማይኖር የጠቅላይ ቤተ ክህነቱና የአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች በተገኙበት ከገዳሙ ተወካዮች ጋራ በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱን”በዋና ዳይሬክተሩ በኩል ገልጧል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ ሚያዝያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ለፓርላማው ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በተያዘው ዓመት የግድቡን ሥራ ከ10 በመቶ በላይ ለማጠናቀቅ ግብ የተጣለ በመኾኑ በግድቡ መሠረት ላይና የወንዙን ውኃ ለመቀልበስ የሚያስችሉ የምንጣሮ፣ ቁፋሮና የአፈር ማስወገድ እንዲሁም የግንባታ ማቴሪያል ዝግጅት ሥራዎች ፕሮጀክቱን ከትግራይ ውኃ ሥራዎች ኮንትራክሽን በተረከበው የግል ኮንትራክተር አማካይነት በመቀላጠፍ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል ለፓርላማው የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት ከአዲሶቹ የስኳር ፋብሪካዎች መካከል በወልቃይትና በሌሎች ሁለት ፕሮጀክቶች የፋብሪካና የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅም ማነስ እንዳጋጠመ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ኣባይ ላጋጠመው የፋብሪካና የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅም ማነስ በምክንያትነት ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑና የተለያዩ ኮንትራክተሮች የመፈጸም አቅም ሳይገነባ በርካታ ሥራዎች መጀመራቸውን ሲኾን ለአቅም ማነሱ በማሳያነት የጠቀሱትም የግድብና የመስኖ መሠረተ ልማቶች፣ የቤቶች ግንባታ፣ የአገዳ ተክል ልማት…ወዘተ በታቀደላቸው ፍጥነት አለመከናወናቸውን ነው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በጠቀሱት ድክመት የሚስማሙ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው የአቅም ማነሱ በግንባታዎች መጓተት ብቻ ሳይኾን ከዘላቂ የልማት አስተምህሮ አኳያ ከአካባቢ ጋራ የተጣጣሙ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ውስንነትም የሚገለጽ ጭምር እንደ ኾነ ይስማማሉ፡፡ ለዚህም መንግሥት በደቡብ ኢትዮጵያ የኦሞ ወንዝ ሸለቆ በ150,000 ሄ/ር መሬት ላይ በሚገነባቸው ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች ሳቢያ የሚፈናቀሉትን ከ40 – 70,000 የሚደርሱ የሙርሲ፣ ቦዲ እና ክዌጌ ጎሳዎች በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ በተቺዎቹ ገለጻ መንግሥት ስለ ልማቱ የአካባቢውን ጎሳዎች በአግባቡ ሳያነጋግርና ሳያማክር ከመኖርያ ቀዬአቸው ማዘዋወሩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንም የሸንኮራ ልማቱ በአካባቢ ላይ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ በውስጥ ሪፖርቱ ማመላከቱ ተዘግቧል፡፡

በአቶ አባይ ሪፖርት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት ባለሞያ “ሌላ ምንም ሳይባል በጥድፊያ ግቡና ሥራ ጀምሩ ተባልን” በማለት ፕሮጀክቱ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚያስከትለው የአካባቢና የማኅበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ እንዳልተሠራ እንዲያውም የግድቡ፣ የሸንኮራ ልማቱ እና ከ7,000 – 8,000 ለሚደርሱ ተፈናቃይ አባ ወራዎች (20,000 ቤተሰቦች) የሚሠሩት የሰፈራ ቦታዎች በየራሳቸው ተነጣጥለው የቆሙ እንጂ ገና የተሟላና የተቀናጀ ዕቅድ እንዳልተቀመጠላቸው ያስረዳሉ፡፡ ግድቡ በውኃ ተሞልቶ ከመስኖ መሠረተ ልማቱ ጋራ ወደ ሥራ የሚገባበትን ጊዜ፣ የሸንኮራ አገዳው ተተክሎ የሚደርስበትን ወራት ከግምት በመውሰድ ፕሮጀክቱ በሂደት (በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ) ወደተሟላ ትግበራ እንደሚገባ ያመለከቱት ባለሞያው፣ ይኸው ክፍተት በዋልድባ ገዳም ላይ ፕሮጀክቱ የሚያሳድረውን ያልተፈለጉ ተጽዕኖዎች የሚቀንሱ ማስተካከያዎች ለማድረግ ዕድል እንደሚሰጥ ይናገራሉ፡፡ www.etsugar.gov.et/corp(Sugar_corporation_site_map)

ማንኛውም ፕሮጀክት ወይም ቴክኖሎጂ ከኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖዎቹ አኳያ የአዛላቂነት ግምገማ ሊሠራለት እንደሚችል የጻፉት በካናዳ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካልጋሪ የኢንቫይሮመንታል ዲዛየን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ በበኩላቸው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ገና ከአሁኑ ወሳኝ የኾነ ማኅበራዊ ተጽዕኖ መፍጠር መጀመሩን በርግጠኝነት መናገር እንደሚቻል ያስቀምጣሉ፡፡ ምሁሩ Akababi – አካባቢ በተሰኘው መጦመሪያቸው www.akababi.org ስለ ወልቃይት የሸንኮራ አገዳ ልማትና የስኳር ፋብሪካፕሮጄክት ባሰፈሩት ጽሑፍ አካባቢያዊ ተጽዕኖ የሚጀምረው በገቢር ከተገለጸ ክሥተት ጋራ ተያይዞ ሲኾን ማኅበራዊ ተጽዕኖ መፈጠር የሚጀምረው ግን በመረጃ ደረጃ ካለ ነገርም ጭምር መኾኑን አስረድተዋል፡፡ የማኅበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ በጣም አስቸጋሪ መስክ ቢኾንም የማንኛውም ልማት ጥቅም የሚለካው ተደምሮ ተቀንሶ ለሰው ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር በመኾኑ የማኅበራዊ አዛላቂነት ግምገማ ወሳኝ ነው።

“የተሳሳተ መረጃም ትክክለኛ መረጃም ተጽዕኖው እኩል ነው” ያሉት ዶ/ር ጌታቸው ኅዳር 24 ቀን 1995 ዓ.ም የወጣውን የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ዐዋጅ በመጥቀስ መንግሥት የፕሮጄክቱ ባለቤትና አስፈጻሚ እንደ መኾኑመጠን ባለድርሻ አካላትን በሙሉ ማሳተፍ እንዳለበት፣ ይህም የሚጀመረው ተገቢውን መረጃ ተደራሽከማድረግ ጀምሮ መኾኑን መክረዋል

ዶ/ር ጌታቸው የጠቀሱት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ዐዋጅ ስለ ሕዝብ ተሳትፎ በሚጠቅሰው ክፍሉ አንቀጽ 15 ቀጥር አንድ ላይ “….ማንኛውም የአካባቢ ተጽዕኖ የጥናት ዘገባ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ በዘገባው ላይ አስተያየትመጠየቅ አለበት፤” ይላል፡፡ በቁጥር ሁለት ላይ ደግሞ “….በአጠቃላይ የሕዝብ በተለይም ደግሞ የፕሮጄክቱአተገባበር ጉዳት ያስከትልባቸው ይኾናል ተብለው የሚገመቱ ማኅበረሰቦች አስተያየት በአካባቢ ተጽዕኖ ጥናትውስጥ መካተቱን እንዲሁም ምርመራው በሚካሄድበት ወቅት መጤኑ መረጋገጥ አለበት፤” ይላል። በዚሁ ዋጅተጽዕኖ በማኅበራዊ እና ባህላዊ ገጽታዎች ላይ የሚከሠት ተከታይ ለውጥን እንደሚያካትት በዐዋጁ አንቀጽአንድ ቁጥር አራት ላይ ተመልክቷል።

በዚህ ምክንያት መንግሥት ልሠራው ያሰብኹት ፕሮጄክት ይህን ይህን ይመስላል፤ በዚህ በዚህ ምክንያትአሁን የተመረጠው መንገድና ቦታ አስፈላጊና አይተኬ ኾኖ (ከኾነ?) አግኝቼዋለሁ፤ ባደረግኹት ጥናትየሚያሳድረው አዎንታዊም አሉታዊም ተጽዕኖ ይህና ይህ ነው፤ ለአሉታዊው ተጽዕኖውም እንዲህ እንዲህ ይነትየመፍትሔ መንገዶች አዘጋጅቼአለኹ፤ ባለድርሻዎች የምትሉት ካለ እነሆ፤ የተሻለ ሐሳብ ካለም ለመስማትናለማየት ለመቀበልም ዝግጁ ነኝ› ማለት አለበት። ይህ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው ዋጅ ላይ እንደተመለከተውበቆይታ በፕሮጄክቱ ምክንያት በቅርብ ርቀት በሚፈጠሩት ከተሞች  ተያያዥ ክሥተቶች ምክንያትየገዳማውያኑ መደበኛ ኑሮ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ተጽዕኖ ከተዳማሪነት እና ለመመለስ ከመቻሉወይም ካለመቻሉ አኳያ መታየት አለበት።

ጦማሪው በጽሑፋቸው እንደሚያብራሩት ባለድርሻን ማሳተፍ ማለት በሥራው ሂደት ላይ ድርሻ የመውሰድያህል ላፊነትን ለባለድርሻው በማሸከም የጋራ የኾነ ሁለንተናዊ አገራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ አንጻርባለድርሻው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲገባበት ማድረግ ነው። የሚሳተፈው አካል ጥቅሙንእንዲያስጠብቅ ድል ከማግኘቱ ጋራ ጥቅሙ በማይጠበቅበት ኔታ ውስጥ እንኳ ነገሩ ተረድቶ በእምነት እንዲቀበለው መንገድ ይከፍትለታል ማለት ነው።

በኢትዮጵያ የአካባቢ፣ የኀይል አቅርቦት እና ፍጆታ ጉዳዮች ላይ የረጅም ጊዜ ጸሐፊ በኾኑት ዶ/ር ጌታቸው እምነት የማንኛውም ክፍል ተነጻጻሪ ጥቅም መለ(!)ካት ያለበት በራሱ መኾን ይገባዋል ይጠቅመዋልየተባለውንም ነገር ራሱ ያለምንም ተጽዕኖ ጥቅሜ ነው እንዲል ለማድረግ ማሳተፍ የግድ ነው። በማሳተፍ ሂደቱደጋፊ፣ አስረጂና ተንታኝ ሊኾን የሚችል አካል ቢኖርም ተደምሮ ተቀንሶ ግን ጥቅሙን የሚለካው ራሱተጠቃሚው ብቻ መኾኑን በተግባር ውቅና መስጠቱ ለሁሉም አካላትና ለሥራውም ተፈጻሚነት እንደሚበጅ በአጽንዖት ይመክራሉ ከወልቃይቱ ፕሮጄክት ጋራ በተያያዘም ያለው ጉዳይ መንግሥት ገና ሥራው መሬትላይ ሳይጀመር ተገቢውን መረጃ ከመስጠት አንሥቶ ሓላፊነቱን መወጣት እንደነበረበት ተችተዋል፡፡ አሁንምቢኾን መንግሥት ቢያንስ የራሱን የጥናት ሰነዶች ይፋ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል

የገዳሙ ክልል ከየት እስከ የት እንደኾነና ስፋቱ ምን ያህል እንደ ኾነ፣ የፕሮጄክቱ ሙሉ ይዘትን ጨምሮ የሚሸፍነው ቦታ ከየት ጀምሮ የት እንደሚያቆም በሚገባ መታወቁ ፕሮጄክቱን አሁን ከታሰበበት ቦታ አንሥቶ ሌላ ቦታ መሥራት ይቻላል ወይስ አይቻልም ለሚለውም ጭምር እንደሚረዳ የዶ/ር ጌታቸው ጽሑፍ ይጠቁማል፡፡

የአካባቢና ኢነርጂ ጉዳዮች ጦማሪው ከማኅበራዊ አዛላቂነት አኳያ በወሳኝ መልኩ ያነሡት የልማት ፕሮጀክቱን አግባብነት የተመለከተ የመረጃ ረኀብ ጉዳይ ጨምሮ ማኅበረ መነኰሳቱ ተስፋ ያደረጉት፣ በርካታ ደጀ ሰላማውያንም የተለያየ አስተያየት የሰጡበት የማኅበረ ቅዱሳን አጥኚ ቡድን ባለፈው ወር መጨረሻ በዋልድባ ገዳምና በፕሮጀክቱ ስፍራ የሳምንት ቆይታ አድርጎ ተመልሷል፡፡

ማኅበሩ የገዳማትንና አድባራትን ችግሮችና የችግሮቻቸውን መንሥኤ በመረጃ በተደገፈ ኹኔታ የመተንተን፣ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ አቅጣጫ ነድፎ የሚንቀሳቀስ ሲኾን ልኡካኑ በዋልድባ ገዳም ተገኝተው ማኅበረ መነኰሳቱ ስለ ፕሮጀክቱ ባላቸው አስተያየት ላይ መወያየታቸው፣ የፕሮጀክት ሓላፊዎችን እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማነጋገራቸው ተዘግቧል፡፡

በፕሮጀክቱ ሰነዶችና የጥናት ቡድኑ አባላት ተዘዋውረው ባሰባሰቧቸው መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀው ሪፖርት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ለማኅበሩ የአመራርና አስፈጻሚ አባላት የጋራ ጉባኤ ቀርቦ ውይይት እንደተካሄደበት ተሰምቷል፡፡ በጽሑፍ፣ በምስልና ድምፅ ማስረጃዎች ተደግፎ የቀረበለትን ዝርዝር ሪፖርት ያዳመጠው የጋራ ጉባኤው የሪፖርቱን ይዘት በተጨማሪ ሞያዊ ምልከታዎች ተንትኖ ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋራ እንዲያቀርብ የሠየመው ሌላ የባለሞያዎች ኮሚቴ በሳምንቱ መጨረሻ ባቀረበው ሐሳብ ላይ ጠንካራ ውይይት ማካሄዱን የማኅበሩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ አባላትና አስፈጻሚዎች እስከ እኩለ ሌሊት የዘለቁ ክርክሮች እንዳደረጉባቸው በተገለጹባቸው ስብሰባዎች ፕሮጀክቱ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚያስከትለው ጉዳትና በጎ ተጽዕኖ በንጽጽር ታይቷል፡፡ ማኅበሩ ፕሮጀክቱን በተሟሉ የአካባቢና የውኃ ሳይንስ ባለሞያዎች ቡድን ዳግመኛ ካላየው በስተቀር ከቀረበው ሪፖርት ጥልቀት ያለው ቴክኒካዊ ዝርዝሮችን ለማግኘት ባለመቻሉ ሪፖርቱን ይፋ ከማድረግ እንዲቆጠብ የሚሉ አቋሞችም መንጸባረቃቸው ተጠቁሟል፡፡ በቀጣይ በመጀመሪያ ለፓትርያሪኩ በእርሳቸውም በኩል/ከእርሳቸው በኋላ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል (ስኳር ኮርፖሬሽን) እና በመጨረሻም ለብዙኀን መገናኛ በሚቀርብበት ኹኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፤ ውሳኔዎችም ተላልፈዋል ተብሏል፡፡

የማኅበሩ ምንጮች ውሳኔዎቹንና የሪፖርቱን ዝርዝር ይዘት ከመናገር ቢቆጠቡም ለደጀ ሰላምበተለያዩ መንገዶች የደረሱ መረጃዎች ሪፖርቱ በዋናነት የሚከተሉትን ነጥቦች መያዙን ያስረዳሉ፡-
·                     ገዳሙ ቤተ ጣዕማ እና ቤተ ሚናስ በተሰኙ ሁለት ማኅበረ መነኰሳት ይዞታ የተከፈለ ነው፤ በቤተ ጣዕማ የመነኰሳቱ ቁጥር ከ200 የማያንስ ሲሆን በቤተ ሚናስ ደግሞ ከ800 – 1000 ይደርሳል፡፡ በቀደሙት ዘመናት በሁለቱ ቤቶች መካከል ስምምነት በመጥፋቱ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በተጣለው ዕጣ ሰፊና ልምላሜ የበዛበት የገዳሙ ክፍል የወደቀው ለቤተ ሚናስ ነበር፡፡ ዛሬ በፕሮጀክቱ የውኃ ግድብ በሚሸፈኑት አካባቢዎችና በሚፈናቀሉት ነዋሪዎች የተነሣ በተጽዕኖ ውስጥ የሚገኘው የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበር ክፍል ነው፡፡
·      የቤተ ሚናስ ማኅበረ መኰሳት በጫና ውስጥ እንዳሉ የሚናገሩ ሲሆን ቃለ ምልልስ በሚያደርጉበት ወቅት መሣቀቅ ይታይባቸው እንደነበር፣ ለፕሮጀክቱም ይኹንታቸውን አለመስጠታቸው ተገልጧል፡፡
·       የፕሮጀክቱ ሓላፊና ሌሎች ባለሥልጣናት ከጅምሩ ማኅበረ መነኰሳቱን እንደ መንግሥት አለማነጋገራቸውና ሳያማክሯቸው ወደ ፕሮጀክት ትግበራው መግባታቸው ስሕተት መኾኑን አምነዋል፡፡ “መነኰሳቱ እግር ላይ ወድቀን ይቅርታ ብንጠይቃቸውም ተቀባይነት አላገኘንም” ያሉት የፕሮጀክቱ ሓላፊ መንግሥት ገዳማውያኑን ስብሰባ በሚጠራበት ወቅት ከቤተ ጣዕማ እስከ 50 መነኰሳት የሚገኙ ሲኾን ከቤተ ሚናስ አንድ ብቻ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ይህም የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት “መንግሥት እያሳደደን ነው፤ ለቤተ ጣዕማም ያደላል” በማለት አመኔታቸውን መሸርሸሩን ከማሳየቱም በላይ በይዞታቸው ላይ ባልተሳተፉበት (ባልተስማሙበት) ውሳኔ እንዲገዙ አስገድዷቸዋል፡፡
·    እኛ ሁሉንም እንደ መነኵሴ ነው የምናያቸው” ያሉት አንድ የፕሮጀክቱ ሓላፊ መነኰሳቱን ሳናሳምን ወደ ልማቱ ከመግባታችን በቀር ፕሮጀክቱ በየትኛውም ሞያዊ መመዘኛ ቢታይ ችግር እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡ የግድቡ ውኃ የገዳሙን መሬት እንደማያጥለቀልቅ፤ በገዳሙ መሬት የሚያልፍ መንገድ፣ የሚካሄድ ሰፈራ ይኹን የፋብሪካ ተከላ እንደሌለ ለቡድኑ ተናግረዋል፡፡
·       በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚቆመው የግድቡ ውኃ 136 ሜትር ወደ ገዳሙ መሬት የሚገባ ሲሆን በዚህም 20 ሄ/ር የገዳሙ መሬት በውኃው ይሸፈናል፡፡ ቡድኑ ለአፈር ምርመራ በሚል ወደ ገዳሙ ክልል ዘልቆ የተጠረገውን ጎዳና እና የተቆፈረ ጉድጓድ (test pit) ተመልክቷል፡፡ መንገዱ አሁን “አገልግሎቱን ጨርሷል” በሚል እንደተዘጋ ለቡድኑ የተነገረ ቢሆንም የግድቡን ዳርና ዳር (Junction) ለመዝጋት በሚካሄደው ቁፋሮ ገዳሙ ዳግመኛ መነካቱ፣ የመንገዱም አገልግሎት መቀጠሉ አይቀርም፡፡
·       በመዘጋ (ከአባ ነጻ በታች) የታመሙ፣ አረጋውያንና ሴቶች መነኰሳዪያት የሚያርፉባቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በ2000 ዓ.ም በሰበካ ጉባኤ እንዲተዳደሩ የወሰነላቸው ሦስት የገዳሙ ይዞታ የኾኑ አብያተ ክርስቲያን (ዕጣኖ ቅድስት ማርያም፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና የአቡነ አረጋዊ አጥቢያዎች) በውኃው የሚሸፈኑ በመኾናቸው ይነሣሉ፡፡ በዚህም ገዳሙ ሰሊጥ የሚያመርትባቸውና ሌሎች የእርሻ ቦታዎች የሚጠፉ በመኾኑ እስከ 40 በመቶ የገቢ ምንጩንና መተዳደሪያውን ያጣል፡፡
·           አባ ነጻ የሚባለው የገዳሙ ክልል የግድቡ ውኃ ለጊዜው የማይደርስበት ቢኾንም ከባሕር ጠለል በላይ የሚገኝበት ከፍታ ለመጥለቅለቅ የሚዳርገው ነው፡፡ ለግንባታው በሚካሄድ ቁፋሮ ምክንያት ከዚህ ቦታ 26 ዐፅሞች ፈልሰው በክብር እንዲያርፉ ስለ መደረጉ ለቡድኑ ተገልጾለታል፡፡
·           ከገዳሙ ይዞታ ውጭ ከ8 – 10 በሚደርሱ የገጠር ቀበሌዎች ከሚነሡት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንና በሺሕ የሚቆጠሩ ምእመናን ምክንያት ገዳሙ እስከ 60 በመቶ የሚኾነውን የምእመናን ድጋፍ ያጣል፡፡
·             ከአካባቢው በርሓማነት አኳያ የግድቡ ውኃ የወባ ወረርሽኝ ሊያባብስ ይችላል፡፡
·            በገዳሙ ክልል ውስጥ የተሰማሩት የጸጥታ ኀይሎች የገዳሙን ሕግና ሥርዐት እየጣሱ ነው፡፡
 ደጀ ሰላም ያነጋገራቸው የውኃ ሀብት ባለሞያዎች (Water Resource Engineers) በቶፖግራፊያዊ ጥናትና ከስኳር ኮርፖሬሽኑ የተሰጡ ይፋዊ መረጃዎችን በመጠቀም የሠሩት ትንተና እንደሚያመለክተው በግድቡ ውኃ የሚሸፈነው የገዳሙ መሬት ከ20 ሄ/ር የበለጠ ነው፡፡ የግድቡ የታችኛው ወለል ከባሕር ጠለል በላይ 810 ሜትር ኾኖ ግድቡ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ የግድቡ ከፍታ 953 ሜትር (በማኅበሩ ሪፖርት 960 ሜትር) ከባሕር ጠለል በላይ የሚገኝ መኾኑን መነሻ በማድረግ በውኃ ሊሸፈን የሚችለውን መሬት ለመገመት በተሠራ ተመሳሳይ መልክአ ምድራዊ ገጽታዎች ትንተና (Contour Map Analysis) ከ1900 – 2800 ሄ/ር የገዳሙ መሬት በውኃው ሊሸፈን እንደሚችል ይናገራሉ (ካርታውን ይመልከቱ)፡፡


ማኅበሩ በሪፖርቱ በሚያቀርባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ከካሳ ጥያቄና የፕሮጀክቱ አካባቢ እንዲለወጥ ከመጠየቅ ጀምሮ እስከ ዲዛየን ማሻሻያ የሚደርስ የጥናት አማራጭ እንዲያቀርብ፣ ገዳማውያኑ ስለ ፕሮጀክቱ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ያላቸው የስምምነት ይኹን የተቃውሞ ሐሳብ የሚደመጥበት፣ አቋማቸውን ያለጫና የሚያሳውቁበት መድረክ እንዲያመቻችም ጠይቀዋል፡፡

ባለሞያዎቹ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለአገሪቱ ተፋሰሶች የሠራውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ማስተር ፕላንበማስታወስ አሁን የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከሚካሄድበት የተከዜ ተፋሰስ ይልቅ አካባቢያዊና ማኅበራዊ አዋጭነት ያላቸው ሌሎች ጥናቶች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም የሚኒስቴሩ ማስተር ፕላን በምዕራብ ትግራይ ዞን ኩፋ ሁመራ እና ታሕታይ አዲያቦ ወረዳዎች የሚገኙ የታችኛው ተከዜ ተፋሰስ የግድብ ልማት አማራጮችን መጠቀም መንግሥት በወልቃይቱ ፕሮጀክት የተነሣ ከሚደርስበት ተቃውሞ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝለት ይናገራሉ፡፡

ኾኖም ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ስፍራ እንደሚቀጥል በቂ ማስረጃዎች በመኖራቸው ገዳሙን አቋርጦ ያልፋል የሚባለው መንገድ ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው ይኾናል፡፡ የመንገድ ሥራን በተመለከተ በቶፖግራፊ ጥናቱ ላይ የሚታየው የዓዲ አርቃይ – ዛሬማ መንገድ ብዙ የመዋቅር ሥራዎችን የማይጠይቅ በመኾኑ በፕሮጀክቱ ሓላፊዎች ዘንድ ግድቡንና የሸንኮራ ልማቱን ለማገናኘት ተመራጭ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ይኹንና በማኅበረ መነኰሳቱ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ቅያሱ በገዳሙ ክልል ስለሚያልፍ የገዳሙን ሕግና ሥርዐት የሚጥሱ፣ ሰላሙን የሚያደፈርሱ ውጤቶችን ያስከትላል፡፡ በመኾኑም ከምሥራቃዊው የዛሬማ – ዓዲ አርቃይ – ማይ ፀምሪ መንገድ ይልቅ ረጅም ቢኾንም ምዕራባዊው የዓዲ ተወልደ መድኅን – መስፍንቶ – ዓዲ ረመፅ መንገድ ተመራጭነት ይኖረዋል፤ ከመስፍንቶ ወይም ከዓዲ ረመፅ አገናኝ መንገዶችን በቀላሉ ወደ ፕሮጀክቱ በመሥራት ወደ ጎንደርም ወደ ሽሬም (ለገበያውም ለተጠቃሚውም) ምርቱን በቀላሉ ማጓጓዝ ይቻላልና፡፡

ሌሎች የጉዳዩ ተከታታዮች መንግሥት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከሚፈልግበት ዓላማና ፍጥነት አኳያ እንዲሁም“ክልላዊ የልማት ስብጥርን ማረጋገጥ” በሚል የያዘውን ዕቅድ በመጥቀስ የባለሞያዎቹን አማራጭ የማይመስል በማለት ያጣጥሉታል፡፡ ለዚህም የስኳር ኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ለፓርማው ባቀረቡት ሪፖርት በተያዘው ዓመት ከ10 በመቶ በላይ የግድብ ሥራውን ለማጠናቀቅ እየተጣደፉ መኾናቸውንና አቶ መለስ ዜናዊ የህወሓትን 37 ዓመት ምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ለወይን መጽሔት የሰጡትን ቃለ ምልልስ ያስታውሳሉ፡፡ አቶ መለስ ለመጽሔቱ እንደተናገሩት በምዕራብ ትግራይ ሥራው በመጣደፍ ላይ የሚገኘው ስኳር ፋብሪካ ከ20 – 30,000 ለሚደርሱ ሥራ ዐጦች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ “ፋብሪካው ለሕዝቡ ቃል የተገባበት ነው፤”ይላሉ ቡድኑ ያነጋገራቸው አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን፡፡
ፕሮጀክቱ በአቶ መለስ እንደተገለጸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተጠቀሰው የሥራ ዐጥ ቁጥር መፍትሔ መኾኑ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነው፡፡ ኾኖም ለፓርቲው ከሚያተርፉለት ፖሊቲካዊ ጥቅሞች የተነሣ ማኅበረ ቅዱሳን በባለሞያዎቹ የተጠቆመውን ይኹን ፕሮጀክቱን በመሠረቱ የሚለውጡ ሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዳያቀርብ ከባድ ጫና እንደሚፈጥርበት ይገመታል፡፡
ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ምክንያት ማኅበሩ በሪፖርቱ ያካተታቸው ‹የመፍትሔ ሐሳቦች› ችግሩን ከመላመድ ጋራ የተቆራኙ (learning to live with the problem) ሳይኾኑ እንደማይቀሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡ “ማኅበሩ መግለጫ መስጠቱ ትርጉም የለውም፤ በመፍትሔነት የተቀመጡት ነጥቦች ከሪፖርቱ ጋራ እንኳ አይመጣጠኑም”ይላሉ ማኅበሩ የሚይዘው የተለሳለሰ አቋም ያሰጋቸው አንድ አባል፡፡ “እውነቱን መግለጽ አለበት፤ እውነቱን መግለጽ ካልቻለ ዝም ቢል/ቢተወው ይመረጣል” ይላሉ ሌላው፡፡ አማካይ አቋም የያዙ አባላትም ማኅበሩ የሚመለከታቸውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች በመያዝ ከመንግሥት አካል ጋራ ተነጋግሮ የሚያሠራውን አማራጭ እንዲያሳውቅ፤ ይህም ካልተሳካ የስምምነትና የልዩነት ነጥቦቹን ይፋ እንዲያደርግ ይጠይቃሉ፡፡
በአንዳንድ የማኅበሩ ምንጮች ጥቆማ ተደርሶባቸዋል የተባሉት የመፍትሔ ሳቦች መንግሥት በውኃ ሙላቱ ለሚፈርሱት ሦስት አብያተ ክርስቲያን ካሳ እንዲከፍል፤ ገዳሙ ለሚያጣው የሰሊጥ እርሻ ትክ መሬት እንዲሰጥ፤ የገዳሙን ምዕራባዊ ገጽ ከብቦ በሚቆመው የግድቡ ውኃ ላይ ተሸጋግረው የሚሰጣቸውን ትክ መሬት ለማልማት የውኃ ላይ ትራንስፖርት የሚያገኙባቸውን ጀልባዎች እንዲያቀርብ፤ ለወባ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከልና ሕክምና ክሊኒክ እንዲቋቁም በሚጠይቁ ነጥቦች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡
የማኅበሩ ሓላፊዎች ሰሞኑን ፓትርያሪኩን ለማነጋገር የያዙት ዕቅድ አቡነ ጳውሎስ በሥጋ ወንድማቸው ሞት በገጠማቸው የቤተሰብ ኀዘን ሳቢያ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ፓትርያሪኩ የሦስት ታናሽ ወንድማቸው በኾኑትና በስኳር ሕመም ላረፉት አባ ሰሎሞን ገብረ ዮሐንስ  ቀብር በዐድዋ እንዳባገሪማ ገዳም የነበሩ ሲኾን ከዚያም መልስ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያ ሓላፊዎችና ጸሐፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሠራተኞች፣ የሌሎች አብያተ እምነት መሪዎችና አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ኀዘናቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ማኅበሩ በሪፖርቱ የደረሰባቸውን ሐቆች ከስኳር ኮርፖሬሽኑ ሓላፊዎች ጋራ ከተነጋገረበት በኋላ ለብዙኀን መገናኛ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
የሪፖርቱ መዘግየት ጥያቄዎች እያስነሣ ባለበት ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ሚያዝያ 9 ቀን 2004 ዓ.ም በነበራቸው የፓርላማ ውሎ፣ “መንግሥት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ነው የሚል ቅሬታ ይደመጣል፤ ምን ምላሽ አሎት?” በሚል ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ “አንዳንድ የሰለፊ እምነት ተከታዮች አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ይታያሉ” በማለት ማኅበረ ቅዱሳንን ከአክራሪ እስላማዊ ኀይሎች ጋራ ደምረው መናገራቸው በማኅበሩ የዋልድባ ገዳም ሪፖርት ላይ የመንግሥትን ፍላጎት ለመጫን ሰበብ እንዳይኾን ብዙዎች መስጋታቸው አልቀረም፡፡ ይህን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የማኅበሩ ምንጮች፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከዋልድባ ገዳም ሪፖርት ጋራ የሚያገናኝ ነገር አለ ብለው እንደማያምኑና ሁለቱም በየራሳቸው መታየት እንደሚገባቸው ያምናሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበሩ ላይ ለተናገሩት መሠረተ ቢስ ውንጀላም ማኅበሩ ማብራሪያ እንዲጠይቅበት፣ የማኅበሩን ተልእኮዎችና አገልግሎቶች በቀጣይነት በመግለጽ የአክራሪነት ውንጀላቸው መሠረተ ቢስ መኾኑን እንዲያጋልጥ እንደሚሹ ይናገራሉ፡፡
‹የሾክ ፈውስ›?
“ዴሞክራሲያዊ እና ልማታዊ መሥመር አራምዳለኹ” የሚለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አክራሪ ኒዮ ሊበራል የሚላቸውን ካፒታሊስት ኀይሎችን ከሚከስባቸው ምክንያቶች አንዱ “ሁሉን ታሪካዊ እና ባህላዊ ዳራ አጥፍተው በቀውሶች ውስጥ ማትረፍ” በሚለው የአስተሳሰብ መዋቅራቸው እንደኾነ በ2ኛ ዓመት ቅጽ 3 ታትሞ የወጣው የግንባሩ አዲስ ራእይ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት ይገልጻል፡፡
በናኦሚ ክሌይን “The Shock doctrine: The rise of disaster capitalism” መጽሐፍ ላይ ተመሥርቶ በመጽሔቱ ላይ የቀረበው ዳሰሳ ለቀውስ የተጋለጠ ማኅበረሰብ ሀብት ንብረቱን፣ ታሪክና ተቋማቱን አሳልፎ እንደሚሰጥ ያብራራል፡፡ “ደሃና ደካማ አገሮችን ከሚዳምጠው፣ የኅብረተሰቡን ባህልና የንቃት ደረጃ ከሚደረምሰው፣ ሀብታሞችን ግን በጥንቃቄ ይዞ ላልተገደበ የካፒታል ስምሪትና ትርፋማነት ከሚያበቃው” የነውጠኛ ኒዮ ሊበራሎች ርእዮተ ዓለማዊ መምሪያ ከኾነው የእነ ሚልተን ፍሪድማን “የኢኮኖሚ ነውጥ ፈውስ” (Economic Shock Treatment) አገሪቱን መጠበቅ ከምንም ነገር ያልተናነሰ ሥራ መኾኑን መጽሔቱ ይገልጻል፡፡ ኢሕአዴግ “ጠንካራ ልማታዊ መንግሥት” የመመሥረት ቅኝት በመያዝ ኒው ሊበራል ፈውሶችን ላለመጋት ጥንቃቄ ማድረጉን የሚገልጸው መጽሔቱ የተቀበላቸው ፈውሶች ቢኖሩም ከልማታዊ መሥመሩ በመነሣት የአገራችንን ዕድገት የማያደናቅፉ መኾናቸውን በማረጋገጥ ብቻ እንደኾነ ያመለክታል፡፡
ጥያቄው ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር በልማታዊ አጀንዳና ስኬት በሚያይበት መነጽር ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ እሴቶች እንደምን ተጠብቀው አልያም ከልማቱ ጋራ ተጣጥመው ይቀጥላሉ? የሚል ነው፡፡ የኢንቫይሮመንታል ዲዛየን ምሁሩ ዶ/ር ጌታቸው እንዲህ ይላሉ፤
የወልቃይቱ ፕሮጄክት [መነጋገርያ] ጉዳይ የኾነው ፕሮጄክቱ ለዋልድባ ገዳማት ካለው “ቅርበት – ርቀት” አኳያ ነው። የዋልድባ ገዳማት ለቅርቡም ለሩቅም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰጡት ከፍተኛ ትርጉም አለ። ዋልድባ የት ነው? ምን ያህል ስፋት አለው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የማይችለውም ኾነ የሚችለው ቢያንስ 44 በመቶ የአገሪቱ ዜጋ በአንድነት ለቦታው መንፈሳዊነት የሚሰጠው ዋጋ ከፍ ያለ ነው፡፡
ከልማት ፕሮጄክቶች ዕቅድና ትግበራ አኳያ መጠናት ካለባቸው ተለዋዋጮች (Variables) አንዱ በታወቁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ መንፈሳዊ እና ሥነ ጥንታዊ ሀብቶች ላይ የሚደርሱት ተጽዕኖዎች እንደ ኾኑ ባለሞያው ይገልጻሉ። ይህም በአገራችን የሕግ ጥበቃ እንዳለው ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡
አቶ መለስ ለወይን መጽሔት እንደገለጹት የምዕራብ ትግራዩ የስኳር ፋብሪካ “የአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚገለጽበት ኢንዱስትሪያዊ ስኬት” ብቻ ሳይኾን ዓመት እስከ ዓመት ሱባኤ በሚያዝበት፣ አባቶች ያለማቋረጥ ከእግዚአብሔር ለሚገናኙበት የዋልድባ ገዳምና 44 በመቶ ኦርቶዶክሳዊ ለኾነው ኢትዮጵያዊ ችግር ኢሕአዴግ የሚያዝዘው “የነውጥ ፈውስ” (Shock Treatment) እንዳይኾን ሊጠነቀቅ ይገባል፤ የ‹ሾክ ፈውስ›ን ኢሕአዴግ ብቻ ሳይኾን ማንም ሊጋተው አይሻምና!! 
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
Advertisements

Read Full Post »ታላቅ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ስለ ታላቁ ዋልድባ ገዳም በሳን ሆዜ 
ቦታው                                                      ቀንና ሰዓት
2500 Masonic Drive                           እሑድ April 29, 2012
San Jose, CA 95125                          ከ 2:00 PM. – 5:00 PM. 

ለተጨማሪ መረጃዎች ይደውሉ
408-582-4299
408-218-6904
408-421-5163
408-417-2329

Read Full Post »አጽመ ቅዱሳንን ማፍለቱ እንደቀጠለ ነውአንድ አድረገን ሚያዚያ 11 2004 ዓ.ም)፡- የዋልድባ ጉዳይን በቅርቡ በአካል ቦታው ድረስ ሄደው የተመለከቱት ሰዎች ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በጥቂቱም ቢሆን ያዩትንና የሰሙትን አካፍለውናል ፤ ቦታው በፖሊሶች እንደተከበበ ገዳሙ የጸሎት ቦታ መሆኑ የቀረ እስኪመስል ድረስ የጦር አውድማ በሚመስል መልኩ በታጠቁ ወታደሮች ተከቧል ፤ አበው መነኮሳቱን ከበአታቸውን እንደ ወንጀለኛ  በጠገበ ወታደር እያዳፉ ሲወስዷቸው በዓይናቸው ተመልክተዋል ፤ በተነሳ ጥያቄ መሰረት ጥይት ተኩሰውባቸዋል ፤ ስውራን አባቶችም እናንተ ባላችሁበት ጸልዩ በማለት ቦታው ላይ በተገኙ ወንድሞቻችን አማካኝነት ለእኛ መልዕክት አስተላልፈውልናል ፤ መንግስትስም ለፕሮጀክቱ መፋጠን መኪኖችን ወደ ቦታው እያመሩ መሆኑን ለማወቅ ችለናል ፤ ባለፈው ቅዳሜ 08-08-2004 ዓ.ም በቪኦኤ ላይ የገዳሙን አንድ አባት አግኝተው እንዳናገሯቸው መንግስት አሁንም አጠናክሮ ስራውን እየሰራ መሆኑን ለቪኦኤ አስረድተዋል ፤ በፊት ቃለ መጠይቅ ያደረጉት አባት አንዳች ስህተት እንዳልሰሩ የተናገሩት ሁሉ ትክክል እንደሆነ ተነግሯቸዋል ፤ ግን ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ አክለው ገልጸዋል፡፡ ብጹእ አቡነ ጳውሎስና ጥቂት ጳጳሳት ለገዳሙ አባቶች ያልተከፈተ ጆሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚሰጡት ወቅታዊ አስተያየት የላይኛውን የተወካዬች ምክር ቤት ወንበር ተቆናጥተውት በኢቲቪ ተመልክተናል ፡፡
ከዚህ በፊት በቦታው ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት አንድ መሀንዲስ መሞቱን ገልጸን ነበር ፤ ከየት እንደመጡ ባልታወቁ ከዱር የወጡ አውሬዎች ቦታው ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችን እየተተናኮላቸው መሆኑን አክለን ገልጸናል ፤ አሁን ደግሞ በቦታው ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ስራውን እየሰሩ ባልታወቀ ምክንያት በየቦታው እየተፈነገሉ ይገኛሉ ፤ በቦታው ላይ የሟች ቁጥር ስድስት ደርሷል ፤ መንግስት ምክንያቱን አልደረሰበትም ፤ መንግስትም ሬሳ ለቀማውን ተያይዞታል ፤ ጊዜው ደርሶ የእነርሱም ሬሳ እስኪለቀም ድረስ ፤ ይህ ነገር በሚዲያ እንዳይወጣ ዝምታን የመረጠ ይመስላል ፤ ወሬው ቢሰማ ለስራው ጥሩ ስላልሆነ ሲሞቱ ብቻ ሬሳ ማንሳትን መርጧል ፤ እስከ አሁን ድረስ  ስድስት ሰዎች ሞተው ተገኝተዋል ፤ ነገ ደግሞ ስራቸውን ከቀጠሉ የባሰ እንደማይመጣ እርግጠኞች አይደለንም ፡፡ እነዚህ ሰዎች በምን ሞቱ ይባላል ?
‹‹ እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ›› ትንቢተ ሚልክያስ 4፤5 ከእኩይ ተግባራችሁ ተመለሱ ፡፡ ‹‹ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል›› የሐዋርያት ሥራ 26፤ 14 ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳውልን በጊዜው እንዲህ ነበር ያለው ፤ አሁንም የመውጊያውን ጫፍ እየነኩ መከራውን እየተቀበሉ ፤ በእነርሱ እየባሰ ይገኛል ፤ ዋልድባን ነክቶ የሰላም አየር መተንፈስ የለም ፤ ለናንተ የምጥ መጀመሪያም  ሊሆን ይችላል ፡፡

መንግስት በህገመንግስቱ ዘወትር ‹‹መንግስት በሐይማኖት ጣልቃ አይገባም›› ይላል ፤ አሁን ግን እየሆነ ያለው የዋልድባ ገዳም አባቶች ምህላ እንኳን በህብረት ሆነው ወደ አምላካቸው እንዳያደርሱ ተከልክለዋል ፤ ምህላ ጸሎት ነው ፤ ጸሎት ማድረግ በመንግስት ከተከለከልን እንዴት መንግስት ጣልቃ አልገባም ማለት እንችላለን ? ፤ የምህላውን ውጤቱን ከኛ ይልቅ እነርሱ የተገነዘቡት ይመስለኛል ፤ የዛሬ 20 ዓመት ገዳሙን የጦር ካምፕ ለማድረግ ሲያስቡ ፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈፅሙ የደረሰባቸው አደጋ ትምህርት ሊሆናቸው አልቻለም ፤

እግዚአብሔር በርካታ ጊዜ በሙሴ አማካኝነት ፈርኦንን ህዝቤን ልቀቅ ብሎ በቀጥታ ነግሮታል ፤ ፈርኦንም ልቡን ክፉኛ አደንድኖ ነበር ፤ በስተመጨረሻም እግዚአብሔር በተዓምር ህዝቡን አስለቅቋል ፤ አሁንም ይህን የስኳር ልማት እንዳትሰሩ ፤ ህገ ወጥ ስራችሁ የገዳሙን ህልውና እንዳይፈታተነው በርካታ ጊዜ በአባቶች እና በምዕመኑ ተመክራችኋል ተዘክራችኋል ፤ ልቦናችሁ ደንቁሮ ዝም ብላችኋል ፤ አሁን አንድ በአንድ እያለ ይለቅማችኋል ፤ እናንተን ሲለቅም እኛን ቁጭ ብለን አንቆጥራለን ፤ የእግዚአብሔርንም ስራ በእምነት እናደንቃለን ፤ ሲጀመር የመጀመሪያው ሰው ሞት ገርሞን ነበር ፤ አሁን ግን ስድስት ሰው መድረሱን ማወቅ ችለናል ፤ እናንተ ልባችሁን ለማደንደን ባሰባችሁ ቁጥር መቅሰፍቱ ከአንድ ሰው ወደ ስድስት ሰው እያደገ ይሄዳል ፤ አምላካችን ዋድባን በተአምር ያስለቅቃችኋ ፤ የአቡነ ተክለኃይማኖት ፤ የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ፤ የአቡነ እስትንፋሰክርስቶስ ፤ የቅድስት አርሴማ አምላክ እኛን አይተወንም ፤ እንደ እኛ ሐጥያት ሳይሆን እንደ አባቶቻችን ጸሎት ብሎ ገዳሙን ከአደጋ እንደሚጠብቀው ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ 1፤14 ላይ ‹‹በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።›› ይላል ፤  እስኪ እኛም በአንድ ልብ ሆነን ስለ ዋልድባ ገዳም በርትተን እየጸለይን  እንትጋ ….የእግዚአብሔርንም እጅ እንጠብቅ ፡፡
የሚቀጥለውን ተዓምር ይጠብቁን

Read Full Post »

የዋልድባ ገዳም ጉዳይ ይበልጡኑ አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል

  • በተለያዩ የአሜሪካን ስቴቶች ውይይቶች፣ ስብሰባዎች፣ ሰላማዊ ሰልፍ ታቅዷል
  • በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን እንዲሁም አባቶች በአጠቃላይ ወደ አንድ አቋም  እየመጡ ነው (መንግስት በአስቸኳይ በዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚያደርሰውን እንግልት፣ ማሳደድ፣ ማፍረስ፣ እንዲያቆም ተጠይቋል)
  • በኒውዮርክ፣ በሳን ሆዜ፣ በቶሮንቶ በቅርብ ቀናት ውስጥ ሰላማዊ ትዕይንት እንዲሁም ውይይቶች እንደሚደረጉ ተነግሮናል፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ገዳመ ዋልድባ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በተለየ መልኩ የሀገርን ሃብትና የወገንን
 ቅርስ ለማጥፋት ከጥፋት ሃይሎች ጋር በመሰለፍ በተለይ ከ1600 ዓመታት በላይ የዘለቀ ታሪክ እና ትውፊት ያለውን የዋልድባ ገዳም አካባቢ የስኳር ፋብሪካ እገነባለሁ፣ የፖርክ ክልል እከልላለሁ በማለት አያሌ ሰቆቃዎችን እያደረሰ ይገኛል። በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በገዳሙ በጸሎት ተወስነው ያሉትን አረጋዊያን ገዳማዊያን በማንገላታት፣ ከጸሎታቸው በማስተጓጎል፣ በውጪ ሚዲያ የተናገሩትን አውጡ በማለት በገዳሙ ቅጽር ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ክብራቸውን በሚነካ መልኩ ወታደሮች ወደ መቅደሱ በጫማቸው በመግባት፣ መናኒያኑን ማንገላታቱን ቀጥለውበታል። ወደ አካባቢው ለጸሎት እንዲሁም ከአካባቢው በረከት ለመቀበል ወደ ቦታው ሄደው የነበሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ብዙ እንግልት እና ማስፈራራት ደርሶባቸው እንደተመለሱ በደጀ ሰላም ድረ ገጽ ወጥቶ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ይህ በሀገራችን መንግስት እያደረሰ ያለውን የሃይማኖት ማጥፋት ዘመቻ በመቃወም በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች፣ ሀገር ወዳድ የቅርስ እና ትውፊት ተቆርቋሪዎች በአሁን ሰዓት ልክ ቀፎው እንደተነካ ንብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከትልቅ እስከ ትንሽ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት፣ ለዚህም አይነተኛ ምስክሮች በመጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እና በኒውዮርክ የኢትዮጵያው ዩናትትድ ኔሽን አምባሳደር ቤት ፊት ለፊት የተደረጉት ሰላማዊ ትዕይንቶችን ተከተትሎ በኮንፈረንስ እንዲሁም በውይይት መድረኮች ላይ እየተዘጋጀ የሰዎች መነጋገሪያ የሆነውን የሰሞንኛ የገዳመ ዋልድባ ጉዳይ እንደሆነ ማንም መገመት እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ ሕዝባዊ ቁጣዎች እና የሕዝብ አቤቱታዎች መንግስት እንደመንግስትነቱ ተመልክቶ መልስ ሊሰጥበት እንዲሁም እያደረገ ካለው የጥፋት ዘመቻ ጊዜ ሳይሰጥ ማቆም እንዳለበት ሊያስገነዝብ የሚችል ይመስለናል።

እነዚህ ሕዝባዊ ትዕይንቶች በመቀጠል በተለያዩ ከተሞች እየተዘጋጁ እንደሆነ ለመገንዘብ ችለናል ከነዚህም በጥቂቱ በቅርቡ በApril 29, 2012 ሳንሆዜ ካሊፎርኒያ ላይ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እንደሚደረግ የደረሰን  ሪፖርት ጨምሮ ገልጿል።
አድራሻውም እንደሚከተለው ነው ከ2:00 – 5:00 PM. የስብሰባ ጥሪ
2500 MASONIC DRIVE
SAN JOSE, CA 95125
ለተጨማሪ መረጃ
408-421-5163, 408-582-4599, 408-218-6904 OR 408-417-2329
በኒው ዮርክ ሲቲ በመጪው ማክሰኞ ጠዋት ከ10:30 AM. ጀምሮ ሰላማዊ ትዕይንት

The Waldorf Astoria
301 Park Avenue

New York City, NY
ለተጨማሪ መረጃ 718-321-3619

በቶሮንቶ ካናዳ በቅርብ ቀን እንደሚደረግ ነግረውናል ሙሉ መረጃው እንደደረሰን እናቀርበዋለን

ለቤተክርስቲያናችን ሰላምን፣ ለሃገራችን እድገትን፣ ለሕዝባችን መልካም አስተዳደርን እንመኛለን
ቸር ያሰማን

Let’s SAVE WALDBA, together.

Read Full Post »

ከዘላለም ወልደኢትዮጵያ


የዋልድባ ገዳማውያንመቼም ልምድ ነውና ልምድ ብቻ አይደለም ባህላችንም ነውና በሰላምታ ልጀምር፡፡ውድ ኢትዮጵውያን ወገኖቼ እንደምን አላችሁ ኑሮስ አንዴት ነው? አለን መቼስ “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” እንደምትሉ ይገባኛል፡፡
ውድ ወገኖቼ እኔ ቃላትን ከቃላት አሳክቼ መፃፍም ሆነ ማንበብ አልችልም፤ ነገር ግን ግድ ሆነብኝና ለትምህርት የምጠቀምባትን ብዕሬን አውጥቼ ይህችን ጦማር ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፡፡ ግን ግራ ገባኝ ለማን ነው ምፅፈው? ምን አገባኝ ልፃፈውና እንደኔ የቆረቆረው ካለ የሃሳቤ ተካፋይ ይሁን ባይሆን እንኳን ህሊናዬ ትንሽ እረፍት ያገኝ ዘንድ እንደ አንድ ዓመት ህፃን ዳዴ ማለት ጀመርሁ፡፡ነገሩ እንዲህ ነው ሰሞኑን ታላቁ የዋልድባ ገዳም ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን የግል መገናኛ ብዙሃን እያሳዩንና እያስነበቡን ይገኛሉ፡፡በእርግጥ ይህ ዜና እውነት ነው፤ ስለሆነም እንዳባቶቻችን “የሰይጣን ጀሮ አይስማው” ብለን ምናልፈው አልሆነም፡፡ይልቅስ ሰውም ሰይጣኑም ከሰማው ዋለ አደረ፡፡


ዋልድባ ገዳም በሰሜን ኢትዮጵያ በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር ወይም በአሁኑ በአማራና  በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ የሚገኝ በመጀመሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ የስደት ዘመን በእርሱ በራሱ የተባረከና በኋላም በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእርሱ በጌታ መሥራችነት የድንጋይ ቆብ ቀርጾ ባመነኮሳቸው መነኮሳት አፅናነት የተመሰረተ ታላቅና ታሪካዌ ገዳም ነው፡፡እመቤታችን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመዋዕለ ስደት ወቅት በኪደተ እግር ከረገጧቸው መካናት አንዱ ሲሆን፣ የእመቤታችን ስም የሚያመሰግኑ ቅዱሳን እንደ አሸን የሚፈሉበት ቦታ መሆኑንም ለእመቤታችን ትንቢት የተናገረው እዚሁ ገዳም ነው፡፡

ይህ ገዳም በስፋቱ፣በመነኰሳት ብዛቱ፣በፍጹማን ባሕታውያን መሸሸጊያነቱ፣ ለስዉራን ቅዱሳን መናኸርያነቱ፣ በበረሃነቱና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ካሉት ገዳማት ታላቁ ገዳም ሲሆን፣ በዓለም ደረጃም ሲታይ ከግብጹ አስቄጥስ ገዳም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ የቅዱሳን በአት  ነው፡፡በአሁኑ ሰአት የተሰወሩ ቅዱሳንን ሳይጨምር ከ3000 በላይ መነኰሳት በቋሚነት ለመላው ዓለምና ለአገራቸው ቀን ከሌሊት ስብሐት ወአኮቴት ወደ አምላካቸው የሚያቀርቡበት ቦታ ነው፡፡

በዚህ ገዳም እልፍ አእላፍ የተሰወሩ መናንያን እንዳሉ በአንድ ወቅት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ስለተሰወሩ መነኮሳት ተጠይቀው የሰጡትን መለስ ማንሳቱ በቂ ነው፡፡እንዲህ ነበር ያሉት፤ “ግብፅ ውስጥ የማይታወቅ (የተሰወረ) መነኩሴ በአሁኑ ጊዜ የለም፤ ኢትዮጵያ ብትሄዱ ግን ብዙ የተሰወሩ መናንያንን ታገኛላችሁ” ነበር ያሉት፡፡እነዚህ የዋልድባ መነኰሳት የሚመገቡት ጌታ የባረከላቸውን በቀን አንድ ጭብጥ ቋርፍ ሲሆን፣ የዓመት ልብሳቸውንም የሚሸፍኑት ከበጎ አድራጊ ምእመናን ከሚያገኙት ስጦታ ነው፡፡ ታዲያ በዓይን የማይታይ ምግብ ይሁን እንጂ ሰማያዊውን ምስጋና እየተመገቡ ፀባ አጋንንቱን፣ ግርማ አራዊቱን በተለይም አንድ ቀን ለመዋል እንኳ የሚከብደውን ያን ከባድ የበረሃ ዋዕይ ታግሰው ለራሳቸውና ለዓለም ድህነትን (ህ ይዋጣል) ሲለምኑ ኖረዋል ፣እየኖሩም ነው፣ይኖራሉም፡፡

የዋልድባ ገዳም እንዲህ በቀላሉ ዘርዝረን የማንጨርሰው ብዙ ታሪክና ቃልኪዳን ያለው ቦታ ነው፡፡ጌታም ዋልድባን “እህልና ኃጢያት አይሻገርብሽ”ብሎ ለመናንያን መጠጊያና የምስጋና ማቅረቢያ ቦታ እንድትሆን ምግባቸውም መራራው ጣፋጭ እንዲሆን በቦታው ተገኝቶ ባርኮላቸዋል፡፡በዚህም ምክንያት ላለፉት እስራ ምእት (2000 ዓመታት) ለገዳሙ መነኰሳት ምግብነት ከተፈቀደው የሙዝ ተክል ውጭ ምንም አይነት እህል መሬቱን ሳይደፍር ቃልኪዳኑ ተጠብቆ እስካሁን ቆይቷል፡፡

በእርግጥ በአንድ ወቅት ባማረው የዋልድባ ሜዳ ላይ እህል አበቅላለሁ ብሎ የተነሳ አንድ ገበሬ  ቃልኪዳኑን (ውግዘቱን ) በመተላለፉ ከእንስሳቱ ጋር እንደ ናቡከደነፆር ወደ ዱር አውሬነት እንደተቀየረ በገዳሙ ውስጥ ከ 20 ዓመት በላይ የቆዩ አንድ አባት ከሁለት ዓመት በፊት ነግረውኛል፡፡በእርግጥ አሁን አሁን በኃጢያታችንና በውሸታችን ብዛት ለአባቶቻችን የተሰጠ ቃልኪዳን ከእኛ እየሸሸ ቢሆንም ቅሉ ስለ ተወሰኑ ደግ አባቶች ሲል ግን እንደማይተወን አምናለሁ፡፡

እንግዲህ በዚህ ገዳም ላይ ነው መንግሥት የሰሜን ተራሮችን አቋርጦ የሚሄደውን የዛሪማን ወንዝ በመጥለፍ ለስኳር ፋብሪካ ግባት የሚሆን የሸንኮራ አገዳ ሰብል ለማልማትና የተወሰነውን ደግሞ  በፓርክነት ከልሎ ለመጠቀም ሥራውን የጀመረው፡፡ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ በግሬደር የቅዱሳን አፅም እየፈለሰ መሆኑ ነው፡፡ ለ2000 ዓመታት ተከብሮ የቆየ ገዳም ነው እንግዲህ እንዲህ አይነት አደጋ የተጋረጠበት፡፡ አባቴ ዱሮ ሲተርት ” ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ “ይል ነበር፡፡

ጎበዝ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶና ጠግቦ ነው ወይ እያደረ ያለው፡፡ኢትዮጵያዊ እኮ ሃብቱ ሳይሆን እምነቱና ባህሉ፣ የአባቶቹ ጸሎት ነው እያኖረው ያለው፡፡አመንም አላመንም የእኛ በሰላም ውሎ ማደር፣ ጤንነት ፣ኑሮ በእኛ ኃይል ብቻ የመጣ ሳይሆን እንደኛ አጥንትና ደም ሳይቆጥሩ ሌት ከቀን በሚፀልዩት አባቶቻችን ጭምር የመጣ ነው፡፡

እስቲ ጎበዝ ቆም ብለን እናስብ፤ ኢትዮጵያ ጣሊያንን ያሸነፈችው ኃይለኛ ጦር ስላላት አይደለም፤ኃይለኛውን አምላክ የሚማጸኑ ቅዱሳን ስላሏት እንጂ፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል ዓድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት እኮ ከሠራዊቱ ጋር በመሆን አብረው ሲያለቅሱ፣ሲፀልዩና ሠራዊቱን ሲናዝዙ ከነበሩት ባህታውያን መካከል አብዛኞቹ የዋልድባ ገዳም መነኰሳት መሆናቸውን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ታዲያ እነዚህን የአገራችን አንጡራ ሃብቶች መንከባከብና መደገፍ ሲገባን ነው መንጥሮ ማጥፋት እንደመፍትሔ እየተወሰደ ያለው፡፡

ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያ በእውነት ይህን ያህል አቅሙ ኖሯት ሁሉን ቦታ አዳርሳ ነው ከዚህ ለመንገድ እንኳ አስቸጋሪ የሆነ ቦታ ላይ ሄዳ የስኳር ፋብሪካ ልገንባ የምትል? ምናልባት “ጠብ ናፈቀኝ እዚያ ማዶ አድረሱኝ” ካልሆነ በቀር፡፡ መች በአገራችን ያሉ ሰፋፊ ወንዞችንና ሜዳዎችን ተጠቅመን መጨረስ ቀርቶ ጀመርናቸውና ነው ቅዱሳን እንዳሸን በፈሉበትና አፅማቸው ባረፈበት ቦታ ላይ ሸንኮራ አገዳ እናልማ የምንል? በእርግጥ ሸንኮራ አገዳው ቢዘራም አይበቅል እንጂ ቢበቅልም ስኳር መስጠቱ ቀርቶ እሬት ይሰጠን ይሆናል፡፡

አንድ መንግሥት የሚመራው ሕዝቡን ከሆነ ያውም በዲሞክራሲ፤ የሕዝቡን ባህል፣ሃይማኖት፣ትውፊት፣አኗኗር የመሳሰሉትን መለያ ባህሪዎች ማክበር አለበት፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋልድባ ገዳም ፈርሶ ስኳር ተመርቶ ሻይ ከሚጠጣ እድሜ ልኩን መራራ ሻይና ቡና ቢጠጣ ይመርጣል፡፡ምክንያቱም ሻይው ጣፍቶት ቢጠጣም ኑሮው መምረሩ አይቀርምና፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በላይ የማንነትና የህልውና ጉዳይ የለምና  ጉዳዩን በቀላል ማየት ያለብን አይመስለኝም፡፡ምናልባት እኔን ውስጤን ያንገበገበኝ ሄጀ ስላየሁት ሊሆን ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህን ነገር ከሸንኮራ አገዳና ከስኳር ባለፈ ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ቢያየውና በጎ ምላሽ ቢሰጥ መልካም ነው፡፡ምናልባት አባቶች በታሪክ መንግሥት ሊወድቅ ሲያምረው ከታቦት ጋር ይጣላል የሚሉት እውነት እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ሰይጣን እንኳን ሊያስበው የማይገባውን ሃሳብ ከማሰብ ጀምሮ በተግባር እያደረጋችሁ ያላችሁ ሰዎች በዚያው ዋልድባ በሚገኘው በማይለበጣ ወንዝ ሄዳችሁ ተጠምቃችሁ ኃጢያታችሁን የማይለበጣ ወንዝ ይፈውሳችሁ እንደሆነ እንጂ የአሁኑ ትውልድም ይሁን የመጭው ትውልድ ይቅር የማይላችሁን ትልቅ ወንጀል እየሠራችሁ መሆኑን ልታውቁት ይገባል፡፡

ስለዚህ “ሳይቃጠል በቅጠል” ነውና ሁሉም ነገር ወደነበረበት ቢመለስ መልካም ይሆናል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ዝምታ መልስ ነው፡፡ይህ ህዝብ ምንም ሞኝ ቢመስልና ዝምታን ቢያበዛ ትናንት ለሃገራቸው ዳር ድንበር፣ታሪክ፣ቅርስና ባህል ሲሉ የዛሬቱን ኢትዮጵያ ከእነማንነቷ ለእኛ ለማውረስ ሲሉ፤ ደማቸውን ያፈሰሱት፣አጥንታቸውን የከሰከሱት የእነአፄ ቴዎድሮስ፣ የእነአፄ ዮሐንስ፣ የእነእምዬ ምኒሊክና የእነቅዱስ ጴጥሮስ ልጅ ነው፡፡ይህ ትውልድ አባቶቹ ያቆዩለትን ታሪክ፣ቅርስ፣ባህል፣ትውፊትና ሃይማኖት ሲመዘበር ዝም ብዬ ልይ ቢል እንኳ አይችልም፤ በአጥንትና በደም ማህተም ያወረሱት ቃልና አደራ አለበትና፡፡

እኔ ይህን የምለው እንደ ሃይማኖተኛ ሁኘ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ነው፡፡ በሃገራችን ለውጥ ሊመጣ የሚችለው እርስ በርስ ከመበላላት ይልቅ እርስ በርስ በወሬ ሳይሆን በተግባር ተቻችለን ያሉንን ታሪካዊ ሃብቶች ስንከባከብ ነው፤ እድገትን ከነሙሉ ታረኩ ልንጎናፀፍ የምንችለው፡፡ይህ ካልሆነ ግን ውሃ በቀጠነ አንድ ሁለት እያልን ታላቅ ታሪካዊና አገራዊ ዳራ ያላቸውን ሀብቶቻችንን ካጠፋን ማን ያውቃል ነገ የእኛ ልጆች ስለአገራቸው ታሪክ ለማወቅ ወደ ምዕራብና ሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሚሄዱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ “መብላት ቢያቅታት በተነችው” የሚባለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ምን አለበት የቱሪስት መስህብነታቸውን በመጠበቅ ታሪካቸውን በጠበቀ መልኩ ብናሳድጋቸው፤ ከእስራኤል ለምን አንማርም ያውም ለማታምንበት ነገር በዓመት ከቅዱሳን መካናት ምን ያህል ገቢ እንደምታገኝ፡፡ አይ ጉድ ሁሉንም ነገር ከአዲስ የመጀመርና አፍርሶ የመሥራት አባዜ ኑሮብን እንጂ ባለን ነገር እየቀጠልን ብንሠራ ኑሮ ዛሬ የት ነበርን?

ልብ ያለው ልብ ይበል ጆሮ ያለው ይስማ
ከመውደሙ በፊት የአገሪቱ ካስማ፡፡
ኦ አንትሙ ሕዝብዬ አንሥኡ እደዊክሙ እንዘ ትብሉ “ኦ እግዚኦ ፈንው እዴከ ኀበ ርስትከ ወውሉድከ” [እጃችሁን ወደ ሰማይ አንሥታችሁ “አቤቱ ወደ ርስትህና ወደ ልጆችህ እጅህን ዘርጋ፤” በሉ፡፡]

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በዚህ አድራሻ zwethiopia@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡

Read Full Post »

var _gaq = _gaq || []; _gaq.push([‘_setAccount’, ‘UA-307455-4’]); _gaq.push([‘_setDomainName’, ‘ipetitions.com’]); _gaq.push([‘_setAllowHash’, ‘false’]); _gaq.push([‘_setAllowLinker’, true]); _gaq.push([‘_trackPageview’]); (function() { var ga = document.createElement(‘script’); ga.type = ‘text/javascript’; ga.async = true; ga.src = (‘https:’ == document.location.protocol ? ‘https://ssl’ : ‘http://www’) + ‘.google-analytics.com/ga.js’; var s = document.getElementsByTagName(‘script’)[0]; s.parentNode.insertBefore(ga, s);})();

Read Full Post »


  • READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • ገዳሙ በከፍተኛ የፖሊስ ኀይል ስምሪት ውስጥ ወድቋል
  •  መነኰሳት በአባትነታቸው አይከበሩም፤ ይዘለፋሉ፤ ይታሰራሉ፤ ጸሎተ ምሕላ በማኅበር እንዳያደርሱ ተከልክለዋል
  • ከአንድ ኪ.ሜ ያላነሰ የገዳሙ መሬት የፕሮጀክቱ አካል ኾኗል
  •  “ስለሚታረሰው አያገባችኹም፤ ስለተተኮሰባችኹና ስለተደበደባችኹት አያገባንም” /አቡነ ኤልሳዕ ለተሳላሚዎቹ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ/። 
  •  “እውነቱን ከማኅበረ ቅዱሳን ልኡካን ሪፖርትና መግለጫ እንጠብቃለን” /ተሳላሚ ምእመናኑ/

(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 8/2004 ዓ.ም፤ April 16/2012)፦ መጋቢት 20 ቀን 2004 ዓ.ም፤ የመድኃኔዓለምን በዓል በአብረንታንት ዋልድባ ገዳም ለማክበር ወደዚያው ለማምራት ተዘጋጅተናል፡፡ መነሻችን ከጎንደር ከተማ ነው፡፡ ካለፉት ዓመታት ጋራ ሲነጻጸር ዘንድሮ  የተሳላሚው ቁጥር አንሶ ይታያል፤ ከጉዟችን በፊት መንገዱ እንደሚዘጋና በርካታ የፌዴራል ፖሊስ ኀይል እንደተላከ አብዝቶ በመሰማቱ የቀረው ሰው ብዙ ነው፡፡

ይኹንና ከከተማው 44 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች፣ 18 ወጣት ማኅበራት እና 10 የጉዞ ማኅበራት የተውጣጡ ምእመናን በሚኒባሶች እና በሁለት አውቶቡሶች ተጓጉዘን ዓዲ አርቃይ ደርሰናል፤ የእግር ጉዞውም የሚጀመረው ከዚያው ከዓዲ አርቃይ ነው፤ መንገዱ እስከ ዋልድባ ገዳም ድረስ ለበረታው የ12 ሰዓት ለሚያዘግመውም ከ16 – 18 ሰዓታት ይወስዳል፡፡
ከዓዲ አርቃይ ተነሥተን ዶንዶሮቃ የሚባል ገዳም ደረስን፤ ዶንዶሮቃ ገዳም የዋልድባ ገዳም አካል ነው፡፡ ከዚህ ጀምሮ ፍተሻው ከባድ ነው፡፡ ፖሊሶቹ መታወቂያ አምጡ እያሉ እንግልት ያደረሱብን፣ ሻንጣችንንና ለመንገድ የያዝነውን ኮቸሮ ሳይቀር የበረበሩት ከዶንዶሮቃ ጀምሮ ነው፤ ስንከላከላቸው መልሳቸው ሌላ ነው፡፡
ዶንዶሮቃ ገዳም ጠበል አለ፤ ከጠበሉ ቦታ ላይ ገላቸውን በሳሙና የሚታጠቡ ሰዎች አገኘን፡፡ ባለማወቅ ስሕተት የሚሠሩ መንገደኞች ናቸው በሚል ልናስተምራቸው ስንሞክር “አያገባችኹም” ብለው ሰደቡን፤ ልብሳቸውን ሲለብሱም እነርሱ [ፖሊሶቹ] ኾነው ተገኙ፤ በያዙት መሣርያ ስላስፈራሩን ለምነናቸው ጉዟችንን ቀጠልንና ማይ ለበጣ ገባን፡፡ ከማይ ለበጣ ወደ ዋናው ገዳመ ዋልድባ – መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደረስን፡፡
በገዳሙ ዙሪያ የፌዴራል ደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች በብዛት ይታያሉ፤ እኔና ጓደኞቼ ለበዓል ወደ ዋልድባ ገዳም ስንመጣ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ ነው፤ ለወትሮው በተወሰነ መልኩ ከሚታየው ሚሊሻ በስተቀር ይህን ያህል ብዛት ያለው ኀይል ገጥሞን አያውቅም፤ አሁን ግን ሁልጊዜም በገዳሙ የሚታየው ሰላማዊ ኹኔታ ጨርሶ ጠፍቶ የጦርነት ድባብ የሰፈነ ነው የሚመስለው፡፡ እንደገባን ያገኘናቸው አባቶችም “ለሚዲያ መግለጫ ሰጥታችኋል፤ በሳተላይት ስልክ ትደዋወላላችኹ” በሚል የታሰሩና የሚፈለጉ አንዳንድ አባቶች እንዳሉ ነው የነገሩን፡፡
መቃብረ አቡነ ሳሙኤልን ተሳለምን፤ በ485 ዓ.ም ከሰሜን ሸዋ ቡልጋ የተነሡ ምእመናን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት መጋቢት 27 ቀን ወደ ዋልድባ ገዳም ከገቡ በኋላ ምእመናኑ “እኛም ከአንተ አብረን ከአንተ ጋራ” ብለው የመድኃኔዓለም ሎሌ መኾናቸውን በገለጹበት ቃል አብረንታንት ተብሎ የተሰየመውን ጌታችንና ከምእመናኑ የተሰወረበትን ሃሌ ሉያ ዋሻ ተመለከትን፡፡

በመቀጠል ማየ ዮርዳኖስ ወደሚባለው የገዳሙ ጠበል ቤት ገብተን ተጠምቀናል፤ ጠበል ቤቱ የራሱ ቅጽር አለው፤ ከጎኑ ለመጠጥ የሚኾን ውኃም ይቀዳበታል፡፡ ወደ ጠበል ቤቱም ይኹን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወዳለበት ቅጽር የሚገባው ጫማ ተወልቆ ቢኾንም ፖሊሶቹ ከነጫማቸው ሲገቡና ሲወጡ ተመልክተናል፡፡ ከትግራይም ከአማራም ገጠሮች ከመጡ ተሳላሚዎች ብዛት የተነሣ ለመጠመቅም ይኹን የሚጠጣ ውኃ ለመቅዳት በሰልፍ ነበር፤ ምእመኑ እየተገፋፋም ቢኾን ራሱን በራሱ ማስተናበር ልማድ ስላደረገው መብዛቱ ችግር አልነበረም፡፡ ዘንድሮ ግን ፖሊሶቹ በሥርዐት ማስከበር ስም ተሰልፎ ከቆመው ሕዝብ መሀል ገብተው በዘፈቀደ መደብደብና የታጠቁትን መሣርያ ቃታ እያቀባበሉ መደንፋትና ማስፈራራት ሥራቸው አድርገውት ነበር፤ ምላሽ በሚሰጣቸው ሰው ላይማ ይብሱ ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን በቦክስ፣ በርግጫ እና በብትር የተመቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ ፖሊሶቹ ጫማቸውን ለምን እንደማያወልቁ የጠየቀ አንድ ልጅ ዐይኑ ላይ በቦክስ መትተውት ፊቱ አብጦ ነበር፡፡ ለመጸዳዳት ወጣ ስንል እንኳ ወከባው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሃይማኖተኝነቱ ቢጠፋ እንዴት ሰብአዊነቱ እንኳ ይጠፋል?

እስከ አሁን ባለው ቆይታችን ብዙ ወከባ ስላየን ወደ ፕሮጀክቱ አካባቢ ተቃርበን ለማየት በነበረን ዕቅድ ላይ ስጋት ገባን፤ የተፈለገውም ይኸው የፍርሃት ቆፈን እንዲያሳስረን ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻ መወሰን ነበረብንና የመጣውን ለመቀበል ቆርጠን 17 ያህል ልጆች በሁለት ቡድን ተከፍለን የውኃው ግድብ ወደሚሠራበት አካባቢ ለመጓዝ ተዘጋጀን፡፡ ከአብረንታንት መድኃኔዓለም ተነሥተን ለሦስት ሰዓት ያህል የእግር ንገድ ተጓዝን፤ አባ ነጻ የተሰኘው ቦታም ደረስን፡፡ ከዚህ በኋላ ግድቡ ወደሚሠራበት የፕሮጀክት ስፍራ ለመድረስ ግማሽ ሰዓት (30 ደቂቃ) ብቻ ነው የወሰደብን፡፡

ግድቡ በሚሠራበት ቦታ ዙሪያ ገባውን ተመለከተን፤ በእይታችን ያረጋገጥነው ሐቅ “አንድ አካፋ አፈር እንኳ አልተዛቀም፤”  እየተባለ ሲሰጡ ከነበሩት መግለጫዎች ጋራ ፈጽሞ የሚጋጭ ነው፡፡ ዶዘሮች፣ ኤክስካቬተር፣ ግሬደር የተባሉት ከባድ ተሽከርካሪዎች በሜዳው ላይ ይታያሉ፡፡ በጄኔሬተር የሚሠራ ባውዛ መብራት ተተክሎ የግድቡ ሥራ ሌት ተቀን እየተፋጠነ መሆኑን ጠይቀን ተረድተናል፡፡ በዚህ ሥራ በዋልድባ በኩል ካለው ተራራ ወደ አባ ነጻ አቅጣጫ ባለው የገዳሙ መሬት ጥምዝምዝ (ዚግዛግ) ጎዳና ያወጣ መሬት ተቆፍሯል፡፡ በዐይን ግምት በዶዘር እየፈረሰ የተቆፈረው መሬት ርዝመት ከአንድ ኪሎ ሜትር አያንስም፡፡ ቁፋሮው የግድቡ መዋቅሮች ግንባታ አካል መኾኑም ተነግሮናል፡፡

ወደ አባ ነጻ ተመለስን፡፡ አባ ነጻ ላይ አባቶችን አግኝተናል፡፡ እዚያው እንደ ቆመን አንድ የፕሮጀክቱ ኤክስካቫተር መኪና መጥታ አፈር እያነሣች ስትቆልል አይተናል፡፡ ስለጉዳዩ አባቶችን ስንጠይቅ “ግድቡ ምን ያህል የደለል ችግር ሊኖረው ይችላል የሚለውን ለመመርመር ተብሎ ነው የሚል ምላሽ ነው የሰጡን” ብለውናል፡፡ የብዙ ቅዱሳን ዐፅም በክብር ከፈለሰበትና ከረገፈበት በዚሁ በአባ ነጻ ከሚገኘው የአቡነ ተስፋ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በቁፋሮው ምክንያት የፈለሱት ዐፅሞች ጉድጓድ ተቆፍሮ በሲሚንቶ በተለሰነ ቤት ውስጥ መከማቸታቸው ተነግሮናል፡፡ በዚሁ ቦታ አሳዛኙ እውነት ግን በአፈር ምርመራ ስም በገዳሙ ሜዳ ላይ ይህን ሥራ ከሚሠሩ ሠራተኞች መካከል አምስቱ ባልታወቀ ምክንያት መሞታቸው ነው፡፡

የዋልድባ መሬት ከመታረሱ አልፎ የሚፈርሱትን እንደ ዕጣኖ ማርያም፣ ጊዮርጊስ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ባንሄድባቸውም ያሉበትን አቅጣጫ ጠቁመው አሳይተውናል፡፡ ግድቡ ሲገደብ ወደ ገዳሙ ያለው መልክአ ምድር በጣም ሜዳማ በመሆኑ እስከ አባ ነጻ ያለውን መሬት ላለመጠቀማቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡ ይህን ያህል ሚልዮን ብር አውጥተው ገድበው ውኃው ወደ አንድ አቅጣጫ ሊሰፋ አይችልም፤ በዋልድባ ወዲህና ወዲያ ማዶ ባሉት ተራሮች መካከል የሚፈሰው የዛሬማ ወንዝ ሲገደብ ውኃው ወዲህም ወዲያም እኩል ስለሚሰፋ ወዲህ ወደ አባ ነጻ አይገቡበትም ብሎ በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፤ ሁሉንም ነገር ሲጀመር ቀስ በቀስ ነውና፡፡ ይህን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ የፕሮጀክቱ ሓላፊዎች አባ ነጻ ላይ ለተሰበሰቡት አባቶች የነገሯቸውን ስንመለከት ነው፡፡ ምንድን ነው ያሏቸው? – “ውኃ እንሰጣችኋለን፤ ሙዝ የምታጠጡበት ከፈለጋችኹ ወደ እናንተም ስለሚመጣ” ነው ያሏቸው፡፡ የአባ ነጻ አባቶችም እንዲህ በማለት ነው የተከላከሏቸው – “አባቶች ያቆዩን በዚህች ውኃ፣ በዚህች ቋርፍ፣ በዚህች ሙዝ ነው፤ እኛም ባለን ነው የምንቆይ፤ ውኃ አንፈልግም አልናቸው፤” ብለውናል፡፡
እኛ ባይናችን እንዳየነው በመጀመሪያ የግድቡ ውኃ በጣም ብዙ ስለሚሆን የገዳሙ መሬት የመጥለቅለቅ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አባቶች በዕጣኖ ማርያም ቤተ ክርስቲያኑ ከሚፈርስበት ላይ የቋርፍ ተክል የሚያለሙበት፣ ሲታመሙ የሚያርፉበት (ሞፈር ቤት የሚባለው) 10 ሄ/ር ያህል መሬት አላቸው፡፡ የፕሮጀክቱ ሓላፊዎች ይህን 10 ሄ/ር መሬት በዕጥፍ አድርገን 20 ሄ/ር ምትክ መሬት ሌላ ቦታ እንሰጣችኋለን እንዳሏቸው የአባ ነጻ አባቶች ነግረውናል፡፡

ከማይ ለበጣ ወዲህ “እህል አይዘራብሽ፤ ኀጢአት አይሻገርብሽ” የሚል ትእዛዝ አለ፤ በፀለምት መሥመር እስከ ዕጣኖ ማርያም መሬቱ በግድቡ ውኃና ብዙ መሬት በሚጠይቀው በሸንኮራ እርሻ ይሞላል፡፡ ለዚህም ሲባል ከ8 – 10 የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎች ቁጥራቸውን ለጊዜው በውል ከማናውቃቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋራ ተነሥተው በሌላ አዲስ መንደር ይሰፍራሉ፡፡ በዚህ ዐይነት በዕጥፍ እንሰጣችኋለን የሚባለው ምትክ መሬት ከገዳሙ በጣም ይርቃል ማለት ነው፡፡ አባቶች ለዚህ ማግባቢያ ያላቸው አስተያየት “አስፋልት ዳር ወስዶ ሊያፈሰን ነው” የሚል ነው፡፡ በእውነቱ በጣም ይረብሻል፡፡ የገጠር አብያተ ክርስቲያናቱ መፍረስ ከሕዝቡ መነሣት ጋራ የተያያዘ ምክንያት ቢሰጠውም በገዳሙ ይዞታ ውስጥ ያለው የቋርፍ ቦታና አብያተ ክርስቲያናቱ መፍረስ ጉዳይ ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል የስኳር ፋብሪካው ሲተከል ከፋብሪካው ግዙፍነት ጋራ ሌሎች የአገልግሎት መስጫ /መገልገያ/ ተቋማት አብሮ ይተከላል፤ መኖርያ ቤት፣ መዝናኛ. . .ወዘተ፡፡ መንገዱ በዛሬማ በኩል ለዋናው ገዳም እንዲቀርብ ኾኖ እየተሠራ ነው፤ አሁንም ለኮንስትራክሽኑ ተብሎ መኪና እየገባ ነው፡፡ ከዚህም ጋራ አብሮ የሚመጣውን ጣጣ መገመት አይከብድም፡፡

እነርሱ እንደነገሩን ከሰሜን ምዕራብ ትግራይሽሬ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የምሥራቃዊ ትግራይዓዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት የፕሮጀክቱ ባለሥልጣናቱ ከማኅበረ መነኰሳቱ ጋራ ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ ማኅበረ መነኰሳቱ በልማት ፕሮጀክቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ አንሥተው ሲሟገቱ ከጳጳሳቱ አንዳቸው ስብሰባውን በጸሎት ከመክፈት ሌላው በጸሎት ከመዝጋት በቀር አንዳችም አስተያየት አለመስጠታቸው አስገራሚ ነበር፡፡

የአባ ነጻ አባቶች እንደሚናገሩት የችግሩ መፍትሔ መታገሥና ጸሎት ማድረግ ነው፡፡ ይኹንና በማኅበር ጸሎተ ምሕላ እንዳያደርጉ በግልጽ ተከልክለዋል፡፡ የበርካታ መነኰሳት በኣት ከውጭ በሩ ተቆልፎ አይተናል፡፡ ከእኒህ መነኰሳት ብዙዎቹ በየዋሻው መሸሸጋቸውን ተረድተናል፡፡ ከማኅበረ መነኰሳቱ ለአንዳንዶቹ እንደመሰላቸውወጣት መጥቶ ጦርነት እንደሚያነሣ፣ መነኰሳቱም ወጣቱም እንደሚያልቁአስበው ነበር፡፡ በቡድን ወደ ስፍራው የሄድነው ተሳላሚዎች ግን የዕለት ውዳሴ ማርያም እየደገምን ጸሎተ ምሕላ እናደርስ ነበር፡፡

ወደ ዋናው የአብረንታንት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመለስን፡፡ እናቶች በአንዲቷ ገጣሚነት እየተመሩ ደረታቸውን እየደቁ፣ ጭናቸውን እየመቱ በትግርኛ የሚቀበሉትን ዜማ ቆመን ስንሰማ ነበር፤ እንዲህ ያለ ዜማ የሰማነው ለክብረ በዓል አኵስም ጽዮን ማርያም ሄደን በነበረ ጊዜ ነው፤ በጣም ያሳዝናል፡፡ አስተርጉመን ስንሰማው “ጌታዬ ለእኛ ስትል ተንገላታኽ፤ ለእኛ ስትል ተሰቅለኽ ሞትኽ” የሚል ነበር፡፡ ከቆይታ በኋላ እኛ ቆመን እያየን ፖሊሶቹ መጥተው መሪዋን እናት ከሌሎች ለይተው እያዋከቡ ይዘዋት ሄዱ፤ የተቀሩትም እናቶች ተበታተኑ፡፡ ለምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ አቀንቃኟ በግጥሞችዋ ውስጥ “ዋልድባ ታረሰ፣ ታረሰ፤ ዛሬ ነው ወይ የሚታረስ፤ ቤትኽን ጠብቅ አንተ፤” የሚሉ ሐረጎችን በመጨመሯ እንደ ኾነ ነገሩን፡፡ የገጠሩን ሰው እንዲህ በዱላ ሲጨረግዱት ስናይ ፍጹም ሰላም በምንጠብቅበት ቦታ ላይ ሰላም እንደሌለ ስንረዳ አዘንን፤ ጸሎተ ምሕላ አደረስን፡፡

ወደ ዋልድባ ገዳም ከገባን ስድስተኛ ቀን ኾኖናል፡፡ በማግስቱ የመድኃኔዓለም ክብረ በዓል ነው፡፡ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ተራ በተራ ለሚከናወነው ጸሎተ ቅዳሴ የዘንድሮ ተረኛ የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት ነበር፡፡ የዛሬ ዓመት የቅዳሴ ተራው የቤተ ጣዕማ ማኅበረ መነኰሳት (ዘጠኝ መለኰት ይላሉ የሚባሉት) ነበር፤ ልማቱን እንደግፋለን እያሉ ስለመፈረማቸው የሚነገርላቸውና በሚዲያ እየቀረቡ የምናያቸው ቤተ ጣዕማዎች ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመው መባዕ ለመሰብሰብ ብቻ ተብሎ የጥንቱን መቃብረ ሳሙኤል ትተው ለእነርሱ በሚያመች ቦታ ሌላ መቃብረ ሳሙኤል ሠርተው ምእመኑ እየተሳሳተ ሲማፀንበትና መባዕ ሲጥልበት ነበር፤ በኋላ ተሳላሚው ወጣት አፈራረሰው፡፡ በዚህ የተነሣ የተፈጠረውን ጠብ የመንግሥት አካል ጣልቃ ገብቶ አስማማቸው ተብሏል፡፡ ዞሮ ዞሮ ያን ያህል ደክመን ሄደን ይህ ዐይነቱ ክፍፍል እዚያ ቦታ ላይ ማየት በተለይ በእምነቱ ላልጠነከረው ምእመን በጣም ጎጂ ነው፡፡

የክብረ በዓሉን ቅዳሴ ጨርሰን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ለመልስ ጉዞ ተነሣን፡፡ ማይ ለበጣ ላይ ገዳሙ ለመድኃኔዓለም በዓል ንፍሮና ጠላ በማዘጋጀት ተሳላሚዎችን ይዘክራል፡፡ እኛም እንደሌላው ተጓዥ እዚያው ቆመን ተዘክረን ማይ ለበጣን ወጥተን ሜዳውን ልናቋርጥ ስንል አንድ አባት በፖሊስ ተይዘው እየተነዱ ሲወሰዱ አየን፡፡ ለነገሩ ቀደም ሲልም የሚፈለጉ፣ የታሰሩም አባቶች እንዳሉ ሰምተናል፡፡

እኚህ አባት ከሕዝቡ ጋራ ተቀላቅለው እየወጡ ነበር፡፡ ፖሊሶቹ ትእዛዝ ተቀብለን ነው በሚል መነኰሱን ወደ ገዳሙ እንዲመለሱ ቢያዝዟቸውም እርሳቸው “መጥሪያ አምጣልኝ፤ አልያ አልሄድም” በሚል ይመላለሳሉ፡፡ ምንድን ነው ብለን ወደያዟቸው አባት ስንቃረብ ፖሊሶቹ “በጭራሽ እንዳትጠጉ! እግር እግርኽን ነው የምሠብርኽ” ብለው መሣርያ አቀባበሉብን፡፡ እንዴ፤ ችግሩ ምንድን ነው? አናግሩን እንጂ እያልን ከመነኩሴው ጋራ እኛም እየተነዳን ስንጠይቃቸው የያዟቸውን አባት ወደ ጥግ አቆሙና ወደ ጎን ይኹን ወደ ላይ ተኮሱ፡፡

ከመሃላችን የተመታብን ሰው እንደሌለ ብናረጋግጥም የመሣርያ ተኩስ ባልጠበቅንበት ቦታ ተኩስ በመስማታችን በጣም አዘንን፤ “ይግደሉን” እያሉ የሚጮኹ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ ከመሀላችን አንድ ሰው በተኩሱ ተመቶ ቢቆስል ወይም ቢሞት ዓለም ይደባለቅ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን በእኛ የተነሳ ችግሩ እንዳይባባስ ውዝግቡን አብርደን ከፊት ቀድመን፣ ፖሊሶቹና የተያዙት አባት ደግሞ ከኋላ ኾነው ወደ ዶንዶሮቃ መጣን፡፡ ዶንዶሮቃ ከደረስን በኋላ የተያዙት አባት “እኔ የመነኰስኹት ለመከራ ነው፤ ይበለኝ፤ ተመለሱ ልጆቼ” በማለት ለእኛ ሰግተው መከታተላችንን እንድናቆም ስለመከሩን፣ ፖሊሶቹም “ምን ይገትርኻል” እያሉ ስላስፈራሩን ክትትላችንን ብናቋርጥም መነኩሴውን እስከ ዶንዶሮቃ ዘልቀው በሚገቡ የገጠር መንገድ ሥራ ድርጅት መኪና ወደ ማይ ፀብሪ ለመውሰድ በሬዲዮ ትእዛዝ ሲቀበሉ ሰምተናቸዋል፡፡ ፖሊሶቹ መነኰሳቱን እንደ አባት ሲያከብሩ ለማየት አልታደልንም፡፡

ማይ ለበጣ እንደተረገው ሁሉ በዶንዶሮቃና በየቀበሌው ሁሉ እንዲሁ የመድኃኔዓለም ዝክር ነበርና እያረፍን ዝክሩን እየቀማመስን ወደ ዓዲ አርቃይ መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ ዓዲ አርቃይ ገብተን ከመካከላችን የጎደለ ሰው እንደሌለ ካረጋገጥን በኋላ ወደ ጎንደር ከመጓዛችን በፊት ዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ ጎራ ብለን የኾነውን ነገር ሁሉ አስረዳን፡፡ የፖሊስ ጣቢያው ዋና አዛዥ ሪፖርታችንን ከሰሙ በኋላ “እንኳን እናንተ በሰላም መጣችኹ፤ ለተተኮሰውም ለድብደባውም ሁሉንም ነገር እንከታተላለን፤” አሉን፡፡

ረፋድ ላይ ከዓዲ አርቃይ ተነሣን፡፡ ደባርቅ ላይ ምሳ አድርገን ጎንደር ገብተን ከመበታተናችን በፊት ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሄደን የኾነውን ሁሉ ማስረዳት አለብን በሚል ተስማማን፡፡ ለምን ቢባል በቀደመው ስብሰባ አልታረሰም ያሉት ገዳም ታርሶ አየን፤ አባቶች ሲንገላቱ ተመለከትን፤ በሽብር ምክንያት ገዳሙን ትተው ሊሰደዱ ነው፤ እንደገና ደግሞ በሰላሙ ቦታ ሰላም አጥተናል፤ በእኛ ላይ ተተኩሶብናል፤ ተደብድበናል፤ በሳምንት የዋልድባ ቆይታችን ጀርባና ትክሻቸውን በብትር የተመቱትን ሳንቆጥር ዐይኑን በቦክስ ተመቶ ፊቱ ያበጠው የጎንደር መድኃኔዓለም ዲያቆን ኹኔታ በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ እኒህን እንኳር ነጥቦች ይዘን ምንም እንኳ በቀደመው ስብሰባ ጥሩ ባይናገሩም ከማንም በላይ ሀገረ ስብከቱ ሓላፊነት አለበት ብለን ሁሉም ተጓዥ ከመኪናው ውስጥ እንዳለ ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አመራን፡፡

በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ስንደርስ ሥራ አስኪያጁን መልአከ ሕይወት ቀለም ወርቅን አገኘናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ከአውቶቡሱ ሲወርድ “ይህ ሽብር መፍጠር ነው” በማለት ሊያናግሩን ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡ ከመካከላችን ስድስት ሰዎች መርጠን ሰደድን፡፡ ለምን እንደመጣን ስንነግራቸው “ስብሰባ ውለን እየወጣን ስለሆነ ብፁዕነታቸው የሚያናግሯችኹ አይመስለኝም” ብለው ጠቅጠቀውን ሊያልፉ ቢሞክሩም ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ከመረጥናቸው ስድስት ሰዎች ሁለቱ እንዲገቡ ተፈቀደ፤ እንደምንም ከጥበቃ ጋራ ተጋፍተን ሦስተኛ ሰው ጨርንና ገባን፡፡

ሲጀመር በታላቁ ገዳም በመሰንበታችን የበለጠውን ቡራኬ እዚያ ካሉት አባቶች ተቀብለናል፤ ብፁዕነታቸውም ወጥተው እንኳን ደኅና መጣችኹ ብለው በቡራኬ ሊቀበሉን ይገባ ነበር፡፡ የእርሳቸው ቡራኬ ይቅርና እኒያ የላክናቸውን ሦስት ልጆች እንኳ በአግባቡ ተቀብለው አላናገሯቸውም፡፡ ልጆቹ አምስት ደቂቃ ያህል ሳይቆዩ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ተመለሱ፡፡ ተወካዮቻችን የገዳሙ መሬት ስለ መታረሱ፣ አባቶች እየተንገላቱ ገዳሙ ሰላም ስለማጣቱ፣ እኛም እንደ ተተኮሰብንና እንደተደበደብን ለሊቀ ጳጳሱ ለማስረዳት ቢሞክሩም የብፁዕነታቸው ምላሽ ግን “ስለሚታረሰው አያገባችኹም፤ ስለተተኮሰባችኹና ስለተደበደባችኹት አያገባንም” የሚል አባታዊነትና መንፈሳዊነት በእጅጉ የጎደለው ንግግር ነበር፡፡

ልጆቹ ይህን አማርኛ ከነገሩን በኋላ ጥቂት የማይባል ተሳፋሪ ከአውቶቡሱ ወርዶ ለመዛለፍ ሞከረ፡፡ በዚህ አኳኋን ብንቆይ ሌላ ነገር ስለሚከተለን “አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፤ መነኰስ ኀያል” የሚለውን የዲያቆን እንግዳወርቅ በቀለ መዝሙር በድምቀት እየዘመርን ወደ መስቀል አደባባይ ሄደን በጸሎት እንደተነሣን በጸሎት ዘግተን ወደ የቤታችን ተበታትነናል፡፡

እኛ በመጨረሻ ነገሩን አወጣነው አወረድነው፤ ከእግዚአብሔር ውጭ ምንም አቅም እንደሌለን ነው የተረዳነው፡፡ በርሓው ላይ ተተኩሶብናል፤ እነርሱም መነኰሳቱም ያልቃሉ እንጂ በሰላም ይመለሳሉ ያለንም አልነበረም፤ በከተማውም እንዲህ አይኾንም ለማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎቻችን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ስትዋረድና ስትናቅ አይተን አናውቅም፡፡ ያለን አማራጭ ጸሎት ብቻ ነው፡፡ ወደ ዘጉ አባቶች ቀርበን የእናንተ ጸሎትኮ አይወድቅም ስንላቸው “እናንተም ባላችኹ አቅም በጸሎት ትጉ” ነው ያሉን፡፡
ቤተ ክህነቱ ቤተ ክሕደት ኾኗል፤ አባቶች እንደመከሩን የመጣውን የሚያቆም ምንም ዐይነት ሰብአዊ ኀይል የለም፤ መፍትሔው ይግባኝ ለክርስቶስ ማለት ብቻ ነው የሚያዋጣው፤ እኒያ የትግራይ እናቶች እንዳሉት መድኃኔዓለም ራሱ በአንዳች ተኣምር ቤቱን ይጠብቃልና!!

ከዚህም ጋራ ደግሞ ሌላው ተስፋችን በዋልድባ ሳለን ያገኘናቸው ከአዲስ አበባና ጎንደር የመጡ የማኅበረ ቅዱሳን ልኡካን ናቸው፡፡ መረጃውና ሪፖርቱ ቀርቦ የማኅበሩ አመራር በጋራ ከተመለከተው በኋላ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አረጋግጠውልናል፡፡ አሁን እኛም ኾነ ሌሎቹ ማኅበራት የእነርሱን ትክክለኛ መግለጫና ሪፖርት እየጠበቅነ ነው፡፡ በእውነቱ እነርሱ የፕሮጀክቱን አካባቢ ለማየት ፈቃድ ስላላቸው፣ ባለሥልጣናቱንና አባቶችን አነጋግረው የድምፅም የምስልም ማስረጃ ስለሚይዙ ከሪፖርታቸው ትልቅ እውነታ ነው የምንጠብቀው፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

Read Full Post »

Older Posts »

አኰቴት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ Akotet Ze-Orthodox Tewahedo

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

አደባባይ

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

አሐቲ ተዋሕዶ AHATI TEWAHEDO

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

ስንክሳር (Senksar)

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ – ማኅበረ ቅዱሳን

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ማኅበረ በዓለ ወልድ ሰሜን አሜሪካ

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

አንድ አድርገን

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views

የዋልድባ ገዳም ታሪካዊ፣ ጥንታዊ፣ ቅዱስ የጸሎት እና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ነው። ቅድስናውንም ከሰው የተሰጠው ሳይሆን በመድኅኒታችን በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተሰጠው ስለሆነ ቦታው ቅዱስ ነው፥ ቅድስናውን ጠብቀን ለትውልድ ማውረስ የእኛ ዋነኛ ዓላማችን ነው።

dejeselam

4 out of 5 dentists recommend this WordPress.com site

%d bloggers like this: