ሢመተ ጵጵስና በትእዛዘ ብልጽግና
#ሰሞኑን በሕገ ወጥ መንገድ የጳጳስ ልብስ ለብሰው ጳጳስ በሉን እያሉ በመንግሥት ወታደሮች ክርስቲያኖችን ሲያስጨፈጭፉ የነበሩ አካላት በቤተ ክህነቱ ግቢ ማንዣበቡን ተያይዘውታል፡፡፡፡
ባለፈው የሐሰት እርቅ ስምምነት ጊዜም ጠቅላዩ ከእነዚህም መካከል የምትሾሙት ይኖራል በማለት ምክር መሰል ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
ሲመተ ጵጵስና እንዴት?
የጵጵስና መሠረቶቹ ሐዋርያት ናቸው፤ ከሐዋርያት መካከል ክርስቶስን ካገኘ በኋላ ወደ ዓለም የተመለሰ ከይሁዳ በቀር አንድም ሐዋርያ የለም፡፡ መላ ሕይወታቸውን፣ መላ ዘመናቸውን የምሥራቹን ወንጌል ለሰው ልጆች ሁሉ ለማዳረስ በመንከራተት፣ በጾም እና በጸሎት፣ በፍጹም ተጋድሎና ትጋት እየኖሩ ምእመናን በበዙባቸው አካባቢዎች ሁሉ ጳጳሳትን እየሾሙ በሰማእትነት አልፈዋል፡፡
የሹመት መሥፈርታቸውም እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥
ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ።›› ማቴ፡ 10፥9
‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።›› ዮሐ፡ 10 11››
‹‹ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛውን ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።› ቲቶ 1፥7-10
‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።›› የሐ፡ ሥራ፡ 20፥ 28
‹‹‹ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ኤጲስቆጶስ ሁኖ የሚሾመው የምእመናን ጠባቂ ነውር የሌለበት ንጹሕ እና ቸር፤ ለዚህ ዓለም የማይጨነቅ፤ ሃምሳ ዓመት የሞላው የወጣትነት ጊዜው ያለፈ፤ ነገረ ሠሪ ያልሆነ፤ በወንድሞች መካከል ሐሰትን የማይናገር ይሆን ዘንድ እንደሚገባው በጌታችን ዘንድ ሰማን፡፡›› ›› ዲድስቅልያ አንቀጽ 4 ቁ 1
ሕዝቡም የሚሾመውን ሰው በስሙ እና በመልኩ በጠባዩም ሊያውቁት ይገባል፡፡ ፍት ነገ 4፥72
‹‹በሚሾምባቸው ሕዝቦች እና በሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ይሁን፤… ኤጲስቆጶስ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በሕዝቡ ምርጫ ይሾም፡፡›› ፍት ነገ 5፥90
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሥርዓተ ሢመትን በዘርፍ በዘርፉ ማቅረብ አይደለም ከላይ ያየናቸው ሐሳቦች ለምናመጣው ሐሳብ መንደርደሪያ ናቸው፡፡
#በመምህር_አምላክ_በሚመጣው_ግንቦት_ሢመተ ኤጲስቆጶሳት_እናዳይካሔድብን
ከሕገወጦቹ ጳጳስ ነን ባይ ግለሰቦች እርቅ ጋር በተያያዘ ከመንግሥትም ከአባቶችም የሰማንው በሚመጣው ርክበ ካህናት ሢመት እንደሚካሄድ ነው፡፡
‹‹መንገድ የጠፋበት ሰው የመጀመሪያ እርምጃው ባለበት መቆም እና ስለመንገዱ መጠየቅ ነው›› ከዚያ ጉዞውን ይጀምራል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአጻዌ ኆኅት እስከ ፓትርያርክ ላሉት የክህነት ማዕርጋት የተሰነደ ሥርዓተ ሢመት ቢኖራትም ተግባራዊነቱ ግን እጅግ የወረደ ነው፡፡
1. ዲቁና የራሱ የሆኑ መሠረታዊ መስፈርቶች ቢኖሩትም አሁን ግን በታላላቅ አድባራት እና ገዳማት የንግሥ በዓላት የተገኘ እና ውዳሴ ማርያም አጥንቶ የተገኘ ሁሉ ያለ ምንም ምርመራ በገፍ ይሾማል፡፡ ከዚህ የተነሳ የቤተ ክርስቲያኗ አማኞች ያልሆኑት ጭምር ተሸመው የሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ ናቸው፡፡
2. በቅስና በኩል ከሚቀድስበት ደብር ዳብዳቤ ያምጣ የሚል መመሪያ ቢተገበርም የዕውቀት መስፈርቱ ከኪዳን እና ከመስተብቁዕ ያላለፈ፤ ቢቻል ብሉያትን ሐዲሳትን አንብቦ የሚተረጉም፤ ያ ባይሆን እንኳን አራቱን ወንጌላት ንባባቸውን ከነትርጓሜያቸው የማያው ሰው ቅስና እንዳይሾም የሚለው ተግባራዊነቱ ተዘንግቶ ያችን የደብር ደብዳቤ ሰው በሰው አስጽፈው የመጡ ሁሉ ቅስና ተቀብለው ይሄዳሉ፡፡
3. አሁን የተነሳንበት ጉዳይ ሢመተ ኤጲስቆሳት በመሆኑ አንዳንድ ማሳያዎችን እንመለከት፡-
ከላይ በመግቢያ የተቀመጡት የመጽሐፍ ቅዱስ እና የቀኖና መጻሕፍት ጥቅሶች እንደሚነግሩን ኤጲስቆስ መላ ሕይወቱን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሰጠ መናኔ ዓለም ከፍቅረ ሢመት፣ ከፍቅረ ንዋይ፣ ከውዳሴ ከንቱ እና ከተድላ ዓለም፤ የግል ቤት ከመገንባት፣ የግል ገንዘብ ከማካበት የራቁ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ከጥንት ጀምሮ የመጣው ሥርዓትም ይሄው ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን
1. የምእመናን ድርሻ እና ተሳትፎ የማይታይበት ሹመት መለመዱ
2. እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ጎሳን መሠረት ያደረገ ሹመት ተግባራዊ መሆኑ
3. ከመናንያን መኰሳት መሆኑ ቀርቶ ምናኔን ትተው ከተማ ከገቡ ግለሰቦች መካከል መመረጡ
4. በባለ ሥልጣናት ጣልቃ ገብነት፣ በሴት ወይዘሮ በወንድ መኰንን አማላጅነት፣ ገፋም ሲል በገንዘብ ጭምር የተድበሰበሰ ሹመት መሾም ከተጀመረ ዋል እድር ብሏል፡፡ የሰሞኑ ግርግርም የዚያ ስህተት ውጤት ነው፡፡
ስለዚህ በመጭው ግንቦትም ሢመት ለማካሄድ መታሰቡ ጥፋቱን ከመድገም ያለፈ ሌላ ረብ ጥቅም የለውም ባይ ነኝ፡፡
ምክንያቱም
1. የቀጣዩ ሹመት ፖለቲካዊ ጫና ያለበት እና ብሔር ተኮተር እንደሚሆን ጭምጭምታዎች መሰማታቸው
2. ሰሞኑን በፍቅረ ሢመት ጦር ተወግተው ከወደቁ ሰዎች መካከል ሹመት እንዲካሄድለት መንግሥት መፈለጉ እና በፈጸሙት በደል እንዲሁም የቀኖና ጥሰት ምክንያት ከነዚህ መካከል አንድ እንኳ ለሢመት የሚበቃ ሰው አለመኖሩ፤ (በፍቅረ ሲመት የተወጋ ደማቸው ሳይደርቅ፣ ትዕቢታቸው ሳይርቅ ጥፋታቸውን ሳያምኑ ከቁምስና እስከ ዲቁና የነበረው ክህነታቸው ተሸሮ እንኳን በድፍረት ቤተ መቅደስ የገቡ ሰው ያስጨፈጨፉ በመሆናቸው ምክንያት)
3. በየጓዳው እና በየሰፈሩ የምንሰማቸው የእኔን ሹሙኝ እና የሹሙልኝ ሽኩቻ በእጅግ በመጨመሩ፤
4. የቤተ ክርስቲያኗ መሠረታዊ ችግር የጳጳሳት እጥረት ባለመሆኑ (ብፁዓን አበው በአንደበታቸው ዓመቱን ሙሉ ወደ ሀገረ ሰብከቱ የማይሄድ ጳጳስ እነዳለ ሲናገሩ ሁላችንም ሰምተናል)
5. ከላይ የተጠቀሱት ከዲቁና ጀምሮ እስከ ፕትርክና ያሉት ያልተከበሩ ሥርዓታት እስኪከበሩ እና ለተገቢው ክህነት ተገቢው ሰው የሚሆንበት የአፈጻጸም መመሪያ እስኪሠራ ድረስ፤
6. ሢመቱ ከተካሄደም ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ችግር እንደ መጨመር በመሆኑ እና ከመናንያን ገዳማውያን መነኰሳት የመምረጥ ዝንባለው ጨርሶ ስለጠፋ፤ በምንም መሥፈር ሢመት መካሔድ የለብንም፡፡
ችግሩ ጎልቶ የታያችሁ ብፁዓን አባቶች፣ የገዳማት አበ ምኔቶች፣ የአብነት መምሀራን፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ ምእመናን በሙሉ ከዚህ በኋላ ተጨማሪ የምናማው አባት እንዲሾም አንፈልግም በማልት ቤተ ክርስቲያናችን እናስከብር፡፡
#በመምህር አምላክ የቀጣዩ ሢመት ይዘግይልን፡፡
መ/ር ኀይለ ማርያም ዘውዱ ዘቦሩ ሜዳ
መጋቢት 21/ 2015 ዓ ም
Leave a comment