- ኮሌጁ እንዲዘጋ የውሳኔ መነሻ የሰጠው ከአቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ ያልወጣው የኮሌጁ ቦርድ ነው
- የኮሌጁ ምግብ ቤት አገልግሎቱን እንዲያቆም በመታዘዙ ደቀ መዛሙርቱ ምሳና ራት ተከልክለው ውለዋል
- አቤቱታቸውን ለመንግሥት አካላት ያሰሙት ደቀ መዛሙርቱ ‹‹ቅ/ሲኖዶስ እና ምእመናን የከፈቱት ኮሌጁ የሚዘጋው በመቃብራችን ላይ ነው!›› በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፤ በአስተዳደር ሕንጻው ዙሪያ የሚያደርጉትን ቁጥጥር አጠናክረዋል
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ ለማስገደድ የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት የፌዴራል ፖሊስ ኀይልን እገዛ መጠየቁ ተገለጸ፡፡
በልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ስም ተፈርሞ የወጣውና ለፌዴራል ፖሊስ እንደተጻፈ በተገለጸው ደብዳቤ÷ ልዩ ጽ/ቤቱ የኮሌጁን ደቀ መዛሙርት በሰላም ነሽነት በመወንጀል ኮሌጁ እንዲዘጋ መወሰኑን ያስታወቀ ሲኾን በዚህም መሠረት ፖሊስ ደቀ መዛሙርቱ ኮሌጁን ለቀው የሚወጡበትን ርምጃ እንዲወስድ እገዛ መጠየቁ ታውቋል፡፡
የልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ የተጻፈው በኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳለ የሚነገረውና በደቀ መዛሙርቱ የችግሩ አካል ተደርጎ የሚተቸው የኮሌጁ ቦርድ ኮሌጁ እንዲዘጋ በሰጠው የውሳኔ መነሻ መኾኑ ተነግሯል፡፡